የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች እንደገና ለማቋቋም፣ ለማደራጀት እና ለማጠናከር የተዘጋጀው አዲስ ረቂቅ አዋጅ ለውይይ

- Advertisement -
Sidebar AD

የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች እንደገና ለማቋቋም፣ ለማደራጀት እና ለማጠናከር የተዘጋጀው አዲስ ረቂቅ አዋጅ ለውይይት ቀረበ

#Ethiopia | ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሀገሪቱ የሕግ ሥርዓት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷንና ያለ ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዋጽኦ የሕግ ጥናት ሙሉ ሊሆን እንደማይችል የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በመድረኩ ገልፀዋል።

ብፁዕነታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሕግና የፍትሕ ሥርዓት መሠረት በመጣል በኩል ታሪካዊ አሻራ አላት ብለዋል።

በተለይም ጥንታዊው “ፍትሐ ነገሥት” መንፈሳዊ ይዘትና መመሪያ ብቻ ያለው ሳይሆን፣ በአሁኑ ዘመን በሀገሪቱ ለሚሠራባቸው የፍትሐ ብሔር እና የወንጀለኛ መቅጫ ሕጎች መነሻ በመሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ብፁዕነታቸው በንግግራቸው አብራርተዋል።

በዚህም የተነሳ ማንኛውም የሕግ ጥናትና ምርምር ሲካሄድ የቤተ ክርስቲያኒቱን የታሪክና የሕግ ማህደር ያላካተተ ከሆነ ሙሉነት እንደሚጎድለው ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሕጎች በዘመናዊው ሥርዓት ውስጥ ያላቸውን ቦታ በተመለከተ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እንዳነሱት፤ አሁን ሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) ሕገ መንግሥት አንቀጽ 34 ንኡስ አንቀጽ 5 የሃይማኖትና የባህል ሕጎችን በግልና በቤተሰብ ጉዳዮች ላይ ዕውቅና እንደሚሰጥና እንደሚፈቅድ ዋቢ አድርገው አስታውሰዋል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የሕግ ታሪክ ሲነሳ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ ሊገባ እንደሚገባና ሕጎቻችንም ከዚህ
ታሪካዊና ነባር ዕሴት የተቀዱ መሆናቸውን በመገንዘብ ሊሠሩ እንደሚገባ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለረጅም ጊዜ ጥናት ሲደረግበት የቆየው ይህ ረቂቅ አዋጅ፤ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 34 ንኡስ አንቀጽ 5 እና 78 ንኡስ አንቀጽ 5 በተደነገገው መሠረት፣ በሃይማኖት ሕግጋት ላይ ተመሥርተው የሚዳኙ የሃይማኖት የፍርድ ተቋማት ዕውቅና ሊሰጣቸው እንደሚችል በሚያስቀምጠው የሕግ ማዕቀፍ ላይ የተመሠረተ ነው።

ይህ አዋጅ ጸድቆ ወደ ተግባር ሲገባ፤ ተከራካሪ ወገኖች በፈቃደኝነት ላይ በተመሠረተ ሁኔታ በጋብቻ፣ በፍቺ፣ በቀለብ አወሳሰን፣ በውርስና ስጦታ ጉዳዮች እንዲሁም ከቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የሥራ ግንኙነትና ከቀኖናዊ አስተምህሮ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ በመንፈሳዊ ፍርድ ቤቶቹ በኩል ዳኝነት እንዲያገኙ ሰፊ ዕድል ይከፍታል በማለት ኣፈ መምህር ኣባ ገብረ ሥላሴ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕግ መምሪያ ዋና ኃላፊ ገልፀዋል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የሕግ ምሁራን በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ የቤተ ክርስቲያኒቱን የፍትሕ ሥርዓት ከማዘመን ባለፈ፣
የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን የሥራ ጫና በማቅለል ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመው፤ አዋጁ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግጋትና በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናዊ ሕጎች (እንደ ፍትሐ ነገሥት እና ዲድስቅልያ) መካከል ያለውን መስተጋብር ግልጽ በሚያደርግበት ሁኔታ ላይ ገንቢ የሕግ ሙያዊ ምክረ ሐሳባቸውን አክለውበታል።

በዛሬው ዕለት የተሰበሰቡት ግብዓቶች ታክለውበት ረቂቅ አዋጁ ይበልጥ ዳብሮ በቅርቡ ለሚመለከተው የመንግሥት የሕግ አውጪ አካል ቀርቦ ዕውቅና ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ አዋጅ መጽደቁ ቤተ ክርስቲያኒቱ በመንፈሳዊ ጠቅላይ ከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ተዋቅራ ተደራሽነቷን እንድታሰፋ ሕጋዊ መሠረት የሚጥል መሆኑም በውይይቱ ላይ ተጠቁሟል።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ የውይይት መርሐግብር ላይ፤ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ አፈ መምህር ኣባ ገብረ ሥላሴ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕግ መምሪያ ዋና ኃላፊ፣ አባቶች፣ ሊቃውንት፣ የፌደራል የመጀመርያ፣ ከፍተኛ ፣ ጠቅላይ እና ሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ታዋቂ የሕግ ምሁራን፣ ጠበቆች፣የፍትሕ አካላት እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu
#EOTC


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: