♦️
#Ethiopia | The Waiting is Over አዎን አሁን ጥበቃው አብቅቷል፤43ኛው የ ESFNA ዓመታዊ ክብረ በዓል ዛሬ በእግር ኳስ ውድድሮች ይፋ ይጀመራል።
ውድድሩን የማስተናገድ ኃላፊነት የወሠደችው ሚኒሶታ ለውድድሩ ስታደርግ የነበረውን ዝግጅቷን አጠናቃ ከሠዓታት በኋላ እንግዶቿን በይፋ መቀበል ትጀምራለች።
በዚህም መሠረት 43ኛው የኢትዮጵያ ስፖርት ፈረዴሬሽን በሠሜን አሜሪካ(Ethiopian Sports Federation in North America) በምህፃረ ቃል (ESFNA) ዓመታዊ የእግር ኳስ ውድድርና ባህላዊ በዓል ከዛሬ ጀምሮ እስከ July 4/2026 በኢገን ሚኒሶታ ግዛት በልዩ ድምቀት የሚካሄድ ሲሆን የመክፈቻ ስነ-ስርዓቱም ነገ ከሠዓት በልዩ ስነ-ስርዓት የሚካሄድ ይሆናል።
43ኛው ዓመታዊ ውድድር እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከተለያዩ የአሜሪካና ስቴቶችና ከካናዳ የሚመጡ ሁለት ቡድኖችን ጨምሮ 32 ቡድኖች የሚሳተፉበት የእግር ኳስ ውድድርና ከኢትዮጵያዊ ባህል፣ ሙዚቃ፣ ምግብ፣ ውዝዋዜ የንግድ ትርኢት ጋር የሚያጣምር ትልቅ የዲያስፖራ ክብረ በዓል ነው።
ዓመታዊ ክብረ በዓሉ ለአረጋውያን የትዝታ መድረክ፣ ለወጣቶች የማንነት መማሪያ፣ ለሕፃናት የኢትዮጵያን ባህል የሚያስተዋውቅ፣የተራራቁና የተነፋፈቁ ቤተሰቦች የሚገናኙበት፣የሚተቃቀፉበት፣ አዳዲስ ወዳጅነቶች የሚመሠረቱበት ከእግር ኳስም በላይ የሆነ ዓመታዊ ፌስቲቫል ነው።
♦️ኢትዮጵያን በአንድ ቦታ፤
ስፖርት እና ባህል ልቦችን በአንድ ገመድ አስረው የሚያቆራኙ ድልድዮች
43ኛው የESFNA ዓመታዊ ፌስቲቫልየሚያስተላልፈው አንኳር መልዕክት ርቀት ኢትዮጵያዊያንን እንደማያራርቅ፣ ባህልና ቋንቋ ልዩነት እንደማያመጡ ይልቁንም ስፖርት እና ባህል ልቦችን በአንድ ገመድ አስረው የሚያቆራኙ ድልድዮች መሆናቸውን የሚያሳዩበት ታላቅ መድረክ ነው።
♦️ውድድሩን የሚያስተናግደው TCO Stadium
ውድድሩን የሚያስተናግደው TCO Stadium የሚባል የMinnesota Vickings የልምምድ ማክል ነው፤ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ጥላ ስር በማሰባሠብ ፍቅራቸውንና ደስታቸውን ስለሀገራቸው ዕድገት የሚመክሩበት የMinnesota Vickings ስታዲየም ከ7,500 እስከ 10,000 በላይ ሠዎችን የማስተናገድ አቅም አለው።
በ2018 የተከፈተው ይህ ስታዲየም ለብዙ አገልግሎት የሚውል አርቲፊሻል ሣር ያለው ሲሆን የህዝብ ቫይኪንጎች የስልጠና ካምፕ ልምምዶችን፣ የሚኒሶታ አውሮራ ኤፍሲ የእግር ኳስ ግጥሚያዎችን፣ የላክሮስ ጨዋታዎችን እና ሌሎች የማህበረሰብ ዝግጅቶችንም የሚያስተናግድ ሲሆን ተሳታፊ ቡድኖች ካረፉበት Omni Viking Lakes በቅርብ ርቀት(Walking Distance)ላይ የሚገኝ መሆኑ ብዙዎችን አስደስቷል።
♦️ESFNA ለወጣቶች የተስፋ ምንጭ፣ ለአረጋውያን የትዝታ፣ለሁሉም ደግሞ የመገናኛና የደስታ በዓል
የሜዳው ፉክክር ልብን ሲያነቃ፣ የባህል ድምቀቱ ኢትዮጵያን በሺዎች ኪሎ ሜትር ርቀትም ቢሆን በአንድ ስፍራ እንደምትገኝ ያመላክታል፤ዓመታዊ ውድድሩ ከውድድርም ባለፈ ለወጣቶች የተስፋ ምንጭ፣ ለአረጋውያን የትዝታ ቤት፣ ለሁሉም ደግሞ የመገናኛና የደስታ በዓል ነው።”
43ኛው የ ESFNA ዓመታዊ ድግስ በማሸነፍና በመሸነፍ ላይ ብቻ ያተኮረ ውድድር አይደለም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ የባህል ኩራትና የወገን ፍቅር የሚገልፁበት ታሪካዊ መድረክም ነው።
♦️በሚኒሶታ “የኢትዮጵያ ቀን”አዋጅ
43ኛው የኢትዮጵያ ስፖርት ፈረዴሬሽን በሠሜን አሜሪካ(Ethiopian Sports Federation in North America) በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚኒሶታ ሲካሄድ እንደ ሀገርም፣እንደ ዜጋም የሚያኮራ ክብርን አግኝቷል፤
የሚኒሶታ ግዛት ገዥ Tim Walz ጁላይ 3/ 2026 ቀን ጀምሮ «የኢትዮጵያ ቀን» (Ethiopian Day) ተብሎ እንዲከበር በይፋ ማወጃቸው ለማህበሩም ለመላው ኢትዮጵያዊያን የኩራትም የክብር መንፈስንም አላብሷል።
በቀድሞው የሀገር ባለውለታ በግብ ጠባቂው ተካበ ዘውዴ በፕሬዝዳንትነት የሚመራውና ጠንካራ የስራ አመራር ቦርድ ያለው አዲስ ስራ አስፈፃሚ ወደ ስልጣን በመጣ በዓመቱ ይሄ ታሪካዊ ውሳኔ መተላለፉ በማህበሩ ጥላ ስር ለተሠባሠቡት አባላት ትልቅ ኩራትና እውቅናንም የሠጠ፣ የኢትዮጵያውያንን ደማቅ ባህል፣ ታሪክ እና በግዛቲቱ ውስጥ ያበረከቱትን ሁለንተናዊ አስተዋፅኦ ይበልጥ ያጎላ ታሪካዊ አጋጣሚም ተደርጎ ተወስዷል።
♦️የዛሬ ውድድሮች ፕሮግራሞች
43ኛው የ ESFNA ዓመታዊ ክብረ በዓል ነገ በልዩ ሴሪሞኒ የሚጀመር ቢሆንም ውድድሩ ከሠዓታት በኋላ በሚካሄዱ ስምንት ውድድሮች የ2026ቱ ዓመታዊ ውድድር በይፋ የሚጀመር ይሆናል።ስድስቱ ጨዋታዎች በTCO Stadium ሁለቱ ደግሞ በሴንት ቶማስ ስታዲየም የሚካሄዱ ይሆናል፤በወጣው ፕሮግራም መሠረት
👉በሁለተኛ ዲቪዚዮን
ዲሲ ዩኒቲ ከ ፖርትላንድ
ሳውዝ ዳኮታ ከ ቶሮንቶ
አበበ ቢቂላ ከ ካልጋሪ
ካንሰስ ሲቲ ከ ሳንሆዜ
👉በአንደኛ ዲቪዚዮን
ቦስተን ከ ዲሲ ስታር
ሎስአንጀለስ ስታር ከ አታላንታ
ሜሪላንድ ከ ሂውስተን
ሲያትል ባሮ ከ ኦኸዮ
እንደሚጫወቱ ከወጣው ፕሮግራም መረዳት የቻለ ሲሆን የመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ በልዩ ፕሮግራም ነገ ከሠዓት በሚደረግ ልዩ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት በይፋ የሚከፈት ይሆናል።
✍️✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ
(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)ከኤገን ሚኒሶታ ግዛት

Source: GetuTemesgen









No comments yet.