የጥበብ ሰው መገናኛ መድረክ በባህርዳር ተካሄደ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ በአርቲስት ወይንሸት አበጀ እና በአርቲስት አሸናፊ ማህሌት አዘጋጅነት በብሉ ናይል ሪዞርት (አቫንቲ) ሰኔ 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ የተካሄደው “የጥበብ ሰው መገናኛ መድረክ” በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ታጅቦ ተጠናቋል።

በመርሃ ግብሩ አንጋፋ የጥበብ ባለሙያዎችና የ2018 ዓ.ም. የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የቴአትርና ሲኒማ ጥበባት ዲፓርትመንት ተመራቂዎች በጋራ የተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎችን ለታዳሚዎች አቅርበዋል።

በዝግጅቱ ላይ ዶክተር አየለ አናውጤ የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና አቶ ገብረማርያም ይርጋ የባህል፣ ኪነ ጥበብና ታሪክ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኃላፊዎቹ ባህርዳርን የጥበብና የጥበበኞች ከተማ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን በማብራራት፣ የአንጋፋ የጥበብ ባለሙያዎች ሚና ለዚህ እቅድ ስኬት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

አንጋፋ የጥበብ ባለሙያዎችም ለዘንድሮ ተመራቂዎች ወደ ሙያው ዓለም ሲገቡ ሊያስተውሏቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች ከሕይወት ልምዳቸው በመነሳት ምክርና ተሞክሮ አካፍለዋል። በተጨማሪም የባህርዳር ከተማ ወጣት ከያኒያን ጥበባዊ ሥራዎቻቸውን ለታዳሚው አቅርበዋል።

በመድረኩ ላይ አርቲስት ወይንሸት አበጀ ለዝግጅቱ ስኬት ላበረከተችው አስተዋፅኦ ከባህርዳር ከተማ ወጣቶች የክብር ስጦታና ሜዳሊያ ተበርክቶላታል። እንዲሁም አርቲስት አሸናፊ ማህሌት እና አንጋፋው አርቲስት ተስፉ ብርሃኔ የሜዳሊያ ሽልማት ተቀብለዋል።

በርካታ ታዳሚዎችን ያሳተፈው መርሃ ግብር በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የውስጥ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግርማው አሸብር ባስተላለፉት የማጠቃለያ መልዕክት ተጠናቋል።

ለዝግጅቱ መሳካት ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አባይ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ ዘመን ኮንስትራክሽን፣ ልህቀት ዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን፣ ብሉ ናይል ሪዞርት እና ቶሎ ትራንስፖርት ድጋፍ አድርገዋል።






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1