አሜሪካ በሩዋንዳ ወርቅ ማጣሪያ ላይ ማዕቀብ ጣለችአሜሪካ በሩዋንዳ የሚገኘውን ጋሳቦ ጎልድ ሪፋይነሪ ጨምሮ ከሶስት የሩዋንዳ ማዕ…

- Advertisement -
Sidebar AD
አሜሪካ በሩዋንዳ ወርቅ ማጣሪያ ላይ ማዕቀብ ጣለች
አሜሪካ በሩዋንዳ የሚገኘውን ጋሳቦ ጎልድ ሪፋይነሪ ጨምሮ ከሶስት የሩዋንዳ ማዕድን ኩባንያዎች እና ከፍተኛ አመራሮቻቸው ላይ አዲስ ማዕቀብ መጣሏን የውጭ ሀብት ቁጥጥር ቢሮ አስታውቋል።
ማዕቀቡ የተጣለባቸው የኩባንያው ሊቀመንበር ዣን ማሊክ ካሊማ እና ዋና ስራ አስኪያጁ ቦስኮ ካዮቦትሲ ሲሆኑ፣ ከእነርሱ ጋር በተያያዘ ቡጋምቢራ ማይንስ፣ዎልፍራም ማይኒንግ እና ርዊንክዋቩ ማይኒንግ ኮርፖሬሽን የተባሉ ተቋማትም በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል።
እንደ አሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ፣ ማጣሪያው በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በኤም23 አማፂያን ቁጥጥር ስር ካሉ አካባቢዎች የሚመጣውን ወርቅ በህገ-ወጥ መንገድ በማሸሽ እና በህጋዊ የንግድ ስርዓት ውስጥ በመደበቅ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
በፈረንጆቹ 2026 መጀመሪያ ላይ ብቻ ከ60 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ በህገ-ወጥ መንገድ መተላለፉ የተጠቆመ ሲሆን፣ ሂደቱም በአንዳንድ አጋጣሚዎች በሩዋንዳ መከላከያ ሰራዊት ጥበቃ ታጅቦ እንደነበር የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ይህ እርምጃ ለአማፂ ቡድኑ የሚፈሰውን የገቢ ምንጭ በማድረቅ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሰላም ስምምነት ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
ማዕቀቡ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደሚሆን የሚጠበቅ ሲሆን፣ የአሜሪካ ዜጎችና ኩባንያዎች ከተጠቀሱት አካላት ጋር የንግድ ግንኙነት እንዳያደርጉ ታግደዋል።
ሩዋንዳ በበኩሏ በአማፂያኑ ላይ ድጋፍ እንደምታደርግ ወይም ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ እንደምታመቻች የሚነገረውን ክስ በይፋ አስተባብላለች።

Source: SeledaPost

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2