♦️
ድፍን 43 ዓመታትን ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ጥላ ስር አሰባስቦ ናፍቆታቸውን የሚወጡበት፣ ባህላቸውን፣ታሪካቸውን፣ቋንቋቸውን፣አልባሳታቸውን ለአዲሱ ትውልድ የሚያስተላልፉበትና ለሌላው ዓለም የሚያስተዋውቁበት ከስፖርትም በላይ ትልቅ ትርጉም ያለው የኢትዮጵያ የስፖርት ፌዴሬሽን በሠሜን አሜሪካ (ESFNA) በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ዓመታዊ ክብረ በዓል በልዩ ድምቀት ተከፈተ።
በመክፈቻው ስነ-ስርዓት በሚኒሶታ ግዛት የሚገኘው የTCO Vicking ስታዲየም ከወትሮው በተለየ በኢትዮጵያውያን ባህል፣ ባንዲራና አንድነት ልዩ ውበት ፈሶበት ውሏል።
የኢትዮጵያ ቀለማት በስታዲየሙ ላይ ሲያበሩ፣ ባህላዊ አልባሳት፣ ዜማዎች እና የደስታ ድምፆች ለተሰበሰበው ሕዝብ ከስፖርትም ባለፈ የታላቅ ክብረ በዓል ድባብን አላብሠውታል።
በሚኒሶታ ግዛት”ኢትዮጵያ”የምትባለው ሀገርን በመፍጠር በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባህላቸውን፣ አንድነታቸውን እና ኩራታቸውን በአስደናቂ ሁኔታ ያሳዩበት ዕለትም ሆኖ ተመዝግቦ አልፏል።
በአጭር ቃል የTCO ስታዲየም በዕለቱ የትርዒትና የባህል ድምቀት ማዕከል ሆኖ ነበር ያለፈው፤የኢትዮጵያ ባንዲራ በክብር ሲውለበለብ ማየት ባህላዊ አልባሳት በውበታቸው የብዙዎችን ቀልብ ይስቡ፣ዐይንንም ይማርኩ ነበር።
በተለይ በዕለቱ የቀረቡትና ኢትዮጵያ የብዙ ባህልና ታሪኮች ባለቤት መሆኗን የሚያሳዩት የአፋርና የጋምቤላ ብሄረሠብ የባህል ሙዚቃዎችና ውዝዋዜዎች፣በአረንጓዴ፣ቢጫና ቀይ ባንዲራችን ያሸበረቁት ታዳጊዎች ያሳዩት የተለያዩ የኪነጥበብ ትርዒቶች መድረኩን ሕይወት ሞልተውበት ለተመልካች ትልቅ ደስታን ለግሠውትም ታይቷል።
በዕለቱ ፕሮግራሙን በታደሙት ላይ የሚታየው የፈገግታ ፊት፣ የአንድነት ስሜት እና የኢትዮጵያዊነት ኩራት ተሳታፊዎቹን በልዩ የደስታ ስሜት አስተሳስሮ ነበር፤
በድምፀ ነጎድጓዱ ታዋቂው የመድረክ መሪ ጋዜጠኛ ወንድወሠን ከበደ መድረኩን በማራኪ ድምፁ ተቆጣጥሮት ተጨማሪ ውበት ፈጥሮለት፣ግርማ ሞገስም አላብሶት ታይቷል፤
በሠልፍ የሚጓዙትን 32 ቡድኖች ሲያሳዩት የነበረው ባህላዊ ጭፈራና የተለያዩ ዳንሶችና ትርዒቶች ለሜዳው ተጨማሪ ውበቶችም ነበሩ።
የዕለቱ የመክፈቻ ፕሮግራም ከመዝናኛነቱ ባሻገር ባህልን የሚያከብር፣ትውልድን ከትውልድ የሚያገናኝ እና የኢትዮጵያውያንን አንድነት በግልጽ የሚያንጸባርቅ የማይረሳ በዓል ሆኖ ማለፉ ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሀገር ዜጎችን ጭምር በግርምት እጃቸውን አፋቸው ላይ እንዲጭኑ አስገድዷል።
በዕለቱ ሌላኛው የመክፈቻው ፕሮግራሙ አካል ሆኖ ያለፈው በውድድሩ ከመሸናነፍ ባለፈ ለወገኖቹ ተቆርቋሪና አጋር መሆኑን ያሳየበት መድረክ መሆኑ ነው፤
የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በሆነው በአቶ ያሬድ ነጋሽ ሃሳቡ የተመዘዘው በአርሲ ዞን በንፁሀን ዜጎች ላይ የደረሠውን ጉዳትና ሞት የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የታሠበ ሲሆን የድጋፍ ማሠበሰቢያ መዘርጋቱንም ይፋ በማድረግ ፌዴሬሽኑ ድርጊቱን ከማውገዝ ባለፊ በዜጎቹ ችግርም ሆነ በደስታ ወቅት ከጎናቸው መሆኑን በተግባር በማሳየቱ ወደ ስልጣን የመጣው አዲሱ አመራር ከየአቅጣጫው የምስጋና ዝናብ እንዲዘንብለት አድርጓል።
በልዩ ልዩ የእግር ኳስ ውድድሮች የተጀመረውና በደማቅ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት በይፋ የተከፈተው 43ኛው ዓመታዊ ክብረ በዓል እስከ ጁላይ 4 እንደደመቀ የሚቀጥል ሲሆን በተለይ በሚኒሶታ ግዛት ገዥ ጭምር ጁላይ 3 የኢትዮጵያዊያን ቀን በሚል የታወጀለት የ “Ethiopian Day” ከወዲሁ ብዙዎች በጉጉት የሚጠብቁት ቀንም ሆኗል።መልካም ክብረ በዓል!!
✍️✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)ኤገን ሚኒሶታ



Source: GetuTemesgen









No comments yet.