በአዲስ አበባ የወጣቶች የኪነ-ጥበብና የፈጠራ ውድድር አውደ ርዕይ ተከፈተ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ “ስብዕና ልማት ለትውልድ” በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የቆየው የወጣቶች የኪነ-ጥበብና የስራ ፈጠራ የውድድር መድረክ እና አውደ ርዕይ በአድዋ ድል መታሰቢያ አደባባይ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አስግደው ኃይለጊዮርጊስ ወጣቶች በከተማዋ የኮሪደር ልማት፣ የስፖርት ማዕከላት ግንባታና በዘመናዊ የኢኮኖሚ መዋቅሮች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ የልማቱ ባለቤትና ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ኃላፊው አክለውም የወጣቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ በላቀ ደረጃ መኖሩ ለሀገራችን ብሩህ ተስፋ ዋስትና ነው በማለት ወጣቶች በስሜታዊነት ሳይሆን በዕውቀት እንዲመሩ እየተሰራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል ተናግረዋል።

በከተማዋ የተገነቡት 114 የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ወጣቱ ከጠባብ አስተሳሰብ ወጥቶ ሰፊ ሀገራዊ ራዕይ እንዲኖረው የሚያግዙ የንቃተ-ህሊና እና የክህሎት ማብሰያ መሳሪያዎች እንደሆኑም በመድረኩ ተነስቷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ክብረአልም ደምሴ በበኩላቸው እነዚህ ማዕከላት ወጣቶች ልምድ የሚለዋወጡባቸው፣ የፈጠራ አቅማቸውን ወደ ስራ የሚቀይሩባቸው እና በስነ-ምግባር የሚታነጹባቸው ዘመናዊ “የልህቀት ማዕከላት” እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምክትል ኃላፊው ወጣቶች በልዩነት ውስጥ አንድነትን በማስቀደም የከተማዋን ሁለንተናዊ የልማት ጉዞ በባለቤትነት እንዲመሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በዝግጅቱ ላይ ባህላዊ ውዝዋዜዎችን፣ ዘመናዊ ዳንስን እና የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን ያካተቱ ውድድሮች እየተካሄዱ ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎን ወጣቶች በክረም በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን የማስተዋውቅ ስራውች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የከተማ አስተዳደሩ ወጣቱን በቴክኖሎጂና በስራ ፈጠራ በማስታጠቅ ተወዳዳሪና አሸናፊ ትውልድ ለመፍጠር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመድረኩ ተመላክቷል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

‎#getutemesgen #getu #ጌጡ







Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1