በአንድ አረንጓዴማ በሆነች የገጠር ከተማ በስሟ ኩየራ በምትባል መንደር ውስጥ ሻርክ የሚባል እና ወይዘሮ ሸዋዬ የሚባሉ እናት አብረው ይኖሩ ነበር። ሻርክ ተራ ውሻ አልነበረም፤ እርጋታው፣ አስተዋይነቱ እና ለአሳዳጊው የነበረው ፍቅር በመንደሩ ሰው ሁሉ ዘንድ የሚደነቅ እና የሚወደድ ነበር። የእሱ አለም… የእሱ መጠለያ እና መላ ህይወቱ ወይዘሮ ሸዋዬ ነበሩ።
ወይዘሮ ሸዋዬ ሻርክን ከትንሽነቱ ጀምረው ነበር ያሳደጉት። በርግጥ ትንሽ ከፍ ብሏል። ጎረቤታችው በፓስፖርት ከውጭ አምጥተውት በሳምንቱ ከዛ ጠፍቶ ሸዋዬ ጋር ገባ። ቢሞክሩት ወስደው ቢያስሩት እሱ ምግብ አልበላም እያለ ገመድ እየበጠሰ መኖርያውን ከሸዋዬ ጋር አደረገ። እሷ ልጆቿ በስራ ምክንያት ውጭ ስለሚውሉ ሻርክ ደግሞ ብቸኝነቷን የሻረላት የልብ ጓደኛዋ ሆነ።
.
ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በሁለቱ መካከል ያለው ትስስር እየጠነከረ መጣ። ወይዘሮ ሸዋዬ ማለዳ ተነስተው ወደ ማሳቸው ሲሄዱ ሻርክ ከፊት ቀደም እያለ መንገዱን ይመራ ነበር። እርሻ ውስጥ ስራቸውን ሲሰሩ እሱ ከዛፍ ጥላ ስር ሆኖ አካባቢውን በትኩረት ይጠብቃል። ማታ ወደ ቤት ሲመለሱም የእርሷን ድካም የሚያውቅ ይመስል እግሯ ስር ተኝቶ እጆቿን በምላሱ ይልስ ነበር። ውጣ ሲባል እንኳ ከሳሎን አይወጣም እያያቸው ነበር የሚውለው።
መንደርተኞቹ ሁልጊዜ፣ “የሸዋዬ ውሻ እኮ ከሰው በላይ ያስባል” ይሉ ነበር። ሻርክ ወይዘሮ ሸዋዬ ደስ ሲላቸው አብሮ ይቦርቃል፣ ሲከፋቸው ወይም ሲደክማቸው ደግሞ ዝም ብሎ አጠገባቸው በመቀመጥ አጋርነቱን ያሳይ ነበር።
ወይዘሮ ሸዋዬ ህይወታቸው ከማለፉ በፊት ባሉት የመጨረሻ ወራት በጠና ታመው አልጋ ላይ ውለው ነበር።
በእነዚያ አስቸጋሪ ቀናት ሻርክ ከቤት አልወጣም። ለህክምና ሆስፒታል ሲሄዱም ተከትሎ ይሄዳል። የምግብ ፍላጎቱ ሙሉ በሙሉ ጠፍቶም ነበር። ስትመለስም ከአልጋዋ ስር አይነሳም ነበር ፣ እሷ በምትሰቃይበት ጊዜ ሁሉ እሱም በሀዘን ያለቅስ ነበር። ወይዘሮ ሸዋዬ የመጨረሻዋን ትንፋሽ ከመውሰዷ በፊት፣ እየተንቀጠቀጠች ያለችውን እጇን ዘርግታ የሻርክን ጭንቅላት ዳሰሰችው። አይኖቿ የእንባ ጠብታ አውርደው ለዘላለም ሲከደኑ፣ ሻርክ ረዥም እና የሚያሳዝን የጩኸት ድምፅ አሰማ ወዳጁ መሄዷን ነፍሱ አውቃው ነበር።
የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ተፈጽሞ መንደርተኛው ሁሉ ወደየቤቱ ሲበተን ሻርክ ግን አብሮ አልተመለሰም። ሻርክ የመቃብር ስፍራ ላይ ልክ በህይወት እያለች እግሯ ስር እንደሚቀመጠው ሁሉ ዛሬም አንገቱን ደፍቶ ተቀምጧል። የመንደሩ ሰዎች ሊወስዱት፣ ምግብ ሊሰጡትና ሊያጽናኑት ሞክረውም ነበር። እሱ ግን ትንሽ ይበላና ትንሽ ቆይቶ ወደ መቃብሩ ይመለሳል ከዛም ቆይቶ ወደቤት።
ዝናብ ሲዘንብ፣ ፀሐይ ሲያቃጥል ሻርክ ከቦታው አይንቀሳቀስም። እሱ አሁንም እየጠበቃት ነው።
ሻርክ በዚህ ድርጊቱ ለሰው ልጆች ትልቅ ትምህርት አስተላልፏል… ፍቅር፣ ታማኝነት እና ትስስር በሞት እንኳ የማይበጠሱ መሆናቸውን። እሱ የአሳዳጊውን አካል አጥቶ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን በእሱ ልብ ውስጥ የእሷ ትውስታ እና ፍቅር እስከ መጨረሻው እስትንፋሱ ድረስ ህያው ሆኖ ይኖራል።
በኤፍሬም ታምሩ
Source: FastMereja









No comments yet.