ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባከናወነችው ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በተለያዩ ጊዜያት ተዘርፈውና ተሰርቀው ከአገር ወጥተው የነበሩ ከ35 በላይ ውድና ታሪካዊ ቅርሶቿን ማስመለስ መቻሏን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር” በሚል በቱሪዝም ዙሪያ ባደረጉት ቆይታ፤ይህ ስኬት መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ ከሰጠው ትኩረት ጎን ለጎን የሀገሪቱን ክብርና የታሪክ ባለቤትነት ለማረጋገጥ የወሰደው ቁርጠኛ እርምጃ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
ከተመለሱት ታዋቂ ቅርሶች መካከል በታሪክ የመጀመሪያዋ በኢትዮጵያውያን የተሠራችው የ”ፀሐይ” አውሮፕላን ከጣሊያን መመለሷን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያውያንን የጀግንነት ታሪክ የሚዘክረው የአፄ ቴዎድሮስ የራስ ፀጉር እንዲሁም በርካታ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት፣ መስቀሎችና ልዩ ልዩ የቤተክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል።
የቅርሶች የማስመለስ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅትም የአፄ ኃይለ ሥላሴን የዙፋን መቀመጫ ጨምሮ ሌሎች ቀሪ ውድ ቅርሶችን ለማስመለስ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ጋር የዲፕሎማሲ ንግግር እየተደረገ መሆኑንጠቁመዋል።
ይህም በቅርቡ ውጤት እንደሚገኝበትና ተጨማሪ የታሪክ ጸጋዎች ወደ ሀገር እንደሚገቡ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
በቅርሶች አያያዝ ላይ በአንዳንድ ወገኖች የሚነሱ ሥጋቶችን በተመለከተም፣ መንግሥት ቅርስን የሚያጠፋ ሳይሆን የጠፋውን የሚመልስና የፈረሰውን የሚያድስ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ቀደም ሲል እንደ እዳ ታይተው ተዘግተውና ተረስተው የነበሩጥንታዊ ቤተመንግሥቶች ዛሬ ላይ ታድሰው ለትውልድ ዕውቀትና ለሀገር ገቢ ምንጭ እየሆኑ መሆናቸውን በአብነት ጠቅሰዋል።
ይህም ለወደፊቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ አዲስ ተስፋን ከመፍጠሩም በላይ፤ትውልዱ የሀገሩን ጥልቅ ታሪክ በቅርበት እንዲያውቅና እንዲያከብር ትልቅ ዕድል የሚከፍት መሆኑን አመላክተዋል።
Ethio Fm
Source: Yeneta Tube









No comments yet.