‎የአትሌቶቹ መፍለቂያ በቆጂ ከተማ ስታዲየም ግንባታ ከምን ደረሰ

- Advertisement -
Sidebar AD


‎#Ethiopia | ኢትዮጵያ ካሏት የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያዎች መካከል ግማሽ ያህሉን ያስመዘገቡት ከአንድ ከተማ የወጡ አትሌቶች ናቸው። ታላላቆቹን የትራክ ጀግኖች አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ አፀደ ባይሳ እና ሲፋን ሀሰንን ጨምሮ ከ60 በላይ አለም አቀፍ ድንቅ አትሌቶችን ያፈራችው በቆጂ ከተማ ነች።

‎ይሁን እንጂ ይህች የአለም አደባባይ ላይ የሀገርን ስም ከፍ ያደረጉ የትራክ ጀግኖች መፍለቂያ ከተማ፣ ራሷ ግን እስካሁን ድረስ ደረጃውን የጠበቀ የሩጫ ትራክ የሌላት ሲሆን፤ የተጀመረው ስታዲየሟም ግንባታው ሳይጠናቀቅ 23 አመታትን አስቆጥሯል።

‎​የበቆጂ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ ብርሃኔ ነገሰ ይህንን የህዝብና የተተኪ አትሌቶች ታላቅ የልማት ጥያቄ ለመመለስና በከተማዋ እየተከናወኑ ስላሉ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ለዝግጅት ክፍላችን ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

‎ከንቲባዋ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት፣ ከተማዋ በአሁኑ ወቅት የአትሌቲክስ ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ደረጃ ከማሻሻል ጀምሮ እስከ ንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመብራትና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ድረስ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።

‎​የበቆጂ ከተማ ስም ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው ታላቁ የአትሌቲክስ ታሪክ ቢሆንም፣ ለአመታት የከተማው ወጣቶችና ተተኪ አትሌቶች የሚለማመዱበት ምቹ ሜዳ አለመኖሩ ትልቅ ክፍተት ሆኖ መቆየቱን ከንቲባዋ አልሸሸጉም።

‎የወጣቶቹና የማህበረሰቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ጥያቄ የራሳቸውም ጥያቄ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ብርሃኔ፣ ዘመናዊ ስታዲየም መገንባት በሚሊዮን ሳይሆን በቢሊዮን የሚቆጠር እጅግ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ በከተማዋ አቅም ብቻ መደገፍ ከባድ እንደሆነ አስረድተዋል።

‎ይሁን እንጂ የህዝቡን የ23 አመታት ታላቅ ትዕግስትና ጨዋነት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በ2019 በጀት አመት ውስጥ ሯጮች ሳይደናቀፉ በቀላሉ ሊለማመዱበት እንዲችሉ ሜዳውን ዳምፕ የማድረግና የማስተካከል ስራ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።

‎ለዚህም ስራ ከበቆጂ የወጡ ተፅዕኖ ፈጣሪና አለም አቀፍ አትሌቶች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ዲፕሎማቶች እንዲሁም ስፖርት ወዳድ ባለሀብቶች የስፖርት ቱሪዝምን ለማሳደግና ተተኪውን ትውልድ ለመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉና ከከተማው አስተዳደር ጋር በባለቤትነት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

‎​ከንቲባዋ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት፣ ከተማዋ የስታዲየሙን ግንባታ ወደ ጎን ባይባልም፤ በአሁኑ ወቅት በከተማው ባለአራት ወለል የከተማ አስተዳደር ህንፃ ግንባታ፣ የወጣቶች ስራ ፈጠራ፣ የኮሪደር ልማት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኒሼቲቭ የሆነውን የመሶብ (የአንድ ማዕከል) አገልግሎት መስጫ ህንጻን የመሳሰሉ አጣዳፊና ከፍተኛ በጀት የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ላይ ትኩረት አድርገዋል።

‎እነዚህ ግንባታዎች እንደተጠናቀቁም ከመንግስት፣ ከክልል፣ ከዞንና ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ወደ ስታዲየሙ ግንባታ ሰፊ እቅድ ይዞ ለመግባት ታስቧል።

‎​የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን በተመለከተ ከሁለት አመት በፊት በከተማዋ ላይ የነበረው ከፍተኛ ችግር በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ መቃለሉን ወይዘሮ ብርሃኔ ነገሰ ገልጸዋል። ከኦሮሚያ ክልልና ከዞን መዋቅሮች ጋር በተደረገ ሰፊ ቅንጅት፣ ባለሙያዎች እስከ ታች ድረስ ወርደው ቀደም ሲል የማይሰሩ የውሃ ጉድጓዶች እንዲጠገኑና አገልግሎት እንዲጀምሩ ተደርጓል። ምንም እንኳን የህዝብ ቁጥር መጨመር የውሃ ፍላጎትን በየቀኑ የሚጨምረው ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የውሃ አቅርቦት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ችግር የሚባልበት ደረጃ ላይ እንዳልሆነ ከንቲባዋ አብራርተዋል።

‎በቆጂ ዙሪያ ያሉ የገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማነት እየመጡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የሚነሱ የውሃ ጥያቄዎችን ለመመለስም፣ ተቋሙ የራሱን በጀት ይዞ ከአመት አመት የማስፋፊያ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥን ጥራት ለማረጋገጥም የማህበረሰብ ፎረም መዘጋጀቱንና ከህዝቡ የተሻለ ግብረ-መልስ መገኘቱን ጠቁመዋል።

‎​የበቆጂ ህዝብ ለረጅም አመታት ሲያነሳው የነበረው ሌላው አንገብጋቢ የመብራት መቆራረጥ ጥያቄም ዘላቂ ምላሽ ማግኘቱን ከንቲባዋ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል። የክልሉ መንግስት በቢሊዮን የሚቆጠር ከፍተኛ በጀት በመመደብ የሃይል ማሰራጫ ጣቢያ ገንብቶ ማጠናቀቁንና በአሁኑ ወቅት ለምረቃ ከመዘጋጀቱም በላይ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል።

‎ይህ ሰብ-ስቴሽን ከ120 እስከ 150 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ የሚገኙ አጎራባች ወረዳዎችን ጭምር በማካተት ሰፊ የሃይል አቅርቦት የዘረጋ በመሆኑ ማህበረሰቡ እጅግ ደስተኛ ሆኗል። ከዚህ ጎን ለጎንም በከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ማስፋፋት ስራዎች ላይ ከፍተኛ መሻሻል የታየ ሲሆን፣ በዚህ በጀት አመት ከተጠናቀቁት አራት መንገዶች በተጨማሪ በአሁኑ ሳምንት አዳዲስ አራት የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ተከፍተው ስራ እየተሰራባቸው ይገኛል።

‎​በመጨረሻም፣ ከንቲባ ወይዘሮ ብርሃኔ ነገሰ የበቆጂና የአካባቢው ማህበረሰብ ላሳየው ሰላም ወዳድነት፣ መቻቻልና አንድነት ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የበቆጂ ህዝብ የተለያዩ ብሄረሰቦች ተከባብረው፣ ባህልና ትውፊታቸውን ጠብቀው የሚኖሩበት የሰላም ተምሳሌት መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፣ ለልማትና ለሰላም ስራ ከመንግስት ጎን ለቆሙት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና የዩኒየን አመራሮች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


‎ጌትነት ተመስገን
‎Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

‎#getutemአesgen #getu #ጌጡ

‎#በቆጂ #የአጀግኖች_መፍለቂያ #የኢትዮጵያ_አትሌቲክስ #የበቆጂ_ስኘጨታዲየም #የልማት_ጎዳና #አርሲ #ኢትዮጵያ #Bekoji #HoxeedmeOfChampions #Ethiopia







Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2