በቬንዙዌላው አስከፊ የመሬት መንቀጥቀጥ ፍርስራሽ ውስጥ ለ32 ሰዓታት የተቀበሩት እናትና የ18 ቀናት ጨቅላ ሕፃን በሕይወት ተረፉ
#FastMereja I በሰሜናዊ ቬንዙዌላ በደረሰው ተከታታይ እና አስከፊ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በፈረሰ የመኖሪያ ሕንፃ ውስጥ ለ32 ሰዓታት ያህል በፍርስራሽ ስር ተቀብረው የነበሩት አንዲት እናት እና የ18 ቀናት ዕድሜ ያላቸው ጨቅላ ልጃቸው በተአምራዊ ሁኔታ በሕይወት ተርፈው መውጣታቸውን ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ቡድኖች አስታውቀዋል።
ዳያና ፓቲኞ የተባለችው እናት ላ ጉዋይራ በተባለችው የባሕር ዳርቻ ከተማ በሚገኘው ባለ 8 ፎቅ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ ሳለች ነበር 7.2 እና 7.5 በሬክተር ስኬል የተመዘገቡት ድርብ የመሬት መንቀጥቀጦች ያጠቁት። ሕንፃው ሲደረመስ ሕፃን ልጇን ኋን ዳቪድን አቅፋ አብራ በፍርስራሹ ውስጥ ብትቀበርም፣ ህጻኑን ከደረቷ ሳትለይ ለሰዓታት መቆየቷንና በሕይወት ለመቆየቷም ዋነኛው ምክንያት እሱ እንደነበር ለቢቢሲ በሰጠችው ቃል ገልጻለች።
የነፍስ አድን ሠራተኞች ፍርስራሹን በመቆፈር መጀመሪያ የ18 ቀናት ጨቅላ ሕፃኑን አውጥተው ለተጨነቀው አባቱ ያስረከቡ ሲሆን፣ ከአንድ ሰዓት ተኩል ተጨማሪ ከፍተኛ ጥረት በኋላ እናቲቱንም በሕይወት ማውጣት ችለዋል። እናቲቱ በጉልበቷ ላይ ስብራት የደረሰባት ቢሆንም፣ ሕፃኑ ግን ምንም ዓይነት ከባድ ጉዳት ሳይደርስበት መተርፉ አነጋጋሪ ሆኗል።
Source: FastMereja









No comments yet.