አዋሽ ባንክ ከታክስ በፊት 40.7 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

- Advertisement -
Sidebar AD

​#FastMereja I አዋሽ ባንክ እ.ኤ.አ. ጁን 30 ቀን 2026 በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በታሪኩ ከፍተኛ የተባለውን እመርታ በማስመዝገብ፣ ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ብር 467.8 ቢሊዮን ማድረሱን የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቁ።

ይህ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የብር 135 ቢሊዮን (41 በመቶ) ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ በባንኩም ሆነ በሀገሪቱ የግል ባንኮች ታሪክ በአንድ ዓመት ውስጥ የተመዘገበ እጅግ ከፍተኛው የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት መሆኑ ተነግሯል።

​የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በተመለከተ፣ መንግሥት ካደረገው የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ ፖሊሲና ባንኩ ከተከተላቸው አሠራሮች በመነሳት ከፍተኛ ዕድገት የታየ ሲሆን፣ የ635 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ጭማሪ በማሳየት በሰኔ 2026 መጨረሻ ላይ ጠቅላላ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱ 2.65 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል። በተመሳሳይ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ብር 622 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ በ38 በመቶ (የብር 10.6 ቢሊዮን) ዕድገት በማሳየት 38.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

ይህ የካፒታል መጠን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለግል ባንኮች ካስቀመጠው ዝቅተኛው ባለ 5 ቢሊዮን ብር መመዘኛ ጋር ሲነጻጸር ከሰባት እጥፍ በላይ ከፍ ያለ በመሆኑ ባንኩ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን የመቋቋም አቅሙ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን ያሳያል ተብሏል።

​በበጀት ዓመቱ አዋሽ ባንክ ከብር 85.37 ቢሊዮን በላይ ጠቅላላ ገቢ የሰበሰበ ሲሆን፣ ጠቅላላ ወጪው ብር 44.62 ቢሊዮን ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህም መሠረት ከቀረጥና ከቅናሽ በፊት ያለው ጠቅላላ ትርፍ (Gross Profit before Provision and Tax) ብር 40.7 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የብር 11.8 ቢሊዮን ብልጫ አለው።

​ባንኩ በአሁኑ ወቅት ከ17 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ማፍራት የቻለ ሲሆን፣ ይህንን ስኬት ያገኘው በሀገሪቱ ባሉት 1,010 መደበኛ ቅርንጫፎች፣ ከ10 በላይ የዲጂታል ቅርንጫፎች (e-branches)፣ ከ1,270 በላይ ኤቲኤሞች፣ ከ18,000 በላይ የባንክ ወኪሎች እንዲሁም እንደ Awash Birr Pro እና Online Banking ባሉ የኦንላይን ቴክኖሎጂዎቹ አማካኝነት ነው።

​አዋሽ ባንክ ባሳየው ተከታታይና እመርታ የተሞላበት የሥራ አፈጻጸም ምክንያት በGlobal Finance ለ5 ተከታታይ ዓመታት “የኢትዮጵያ ምርጥ ባንክ” ተብሎ የተመረጠ ሲሆን፣ የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱም በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው የዓለም ባንክና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ስብሰባ ወቅት እንደሚፈጸም ታውቋል።

ባንኩ ከንግድ ሥራው ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በተለያዩ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ችግሮች ለተጠቁ የሕብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ የሚውል የብር 500 ሚሊዮን ወጪ ማድረጉም በመግለጫው ተጠቅሷል።

#ቢዝነስ






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2