#Ethiopia | የሀገሪቱን የቱሪዝም መዳረሻዎች በዘመናዊ መንገድ ለዓለም ለማስተዋወቅና የመረጃ ልውውጡን በተቀናጀ ስልት ለመምራት የሚያስችል የቱሪዝም ኮሙኒኬሽን ስልጠና በአዳማ ከተማ የተካሄደ ሲሆን፣ በዚሁ መድረክ ላይ የቱሪዝም ሚዲያ ፎረም በይፋ ተመስርቷል።
የፌደራልና የክልል የቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን እንዲሁም የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ጋዜጠኞችንና ኃላፊዎችን ያሳተፈው ይህ መርሃ-ግብር፣ በዘርፉ የሚታየውን የተበታተነ የኮሙኒኬሽን ስራ በማስቀረት የተቀናጀ የቱሪዝም ዲፕሎማሲ ለመገንባት ያለመ ነው።
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሴ ክብሩ፣ መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከሀገሪቱ አምስት ዋና ዋና የኢኮኖሚ አመንጭ ዘርፎች ውስጥ አንዱ አድርጎ እየሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።
በርካታ አዳዲስ መዳረሻዎችን የማልማትና በነባሮቹ ላይ እሴት የመጨመር ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፣ እነዚህን ጸጋዎች በዘመናዊ ስልት ለአለም ማስተዋወቅና የሀገርን በጎ ገጽታ መገንባት የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሊወጡት የሚገባ ዋነኛ ሀገራዊ ኃላፊነት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ለተሳታፊዎቹ ስልጠና የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የቱሪዝም ሚዲያ ስራ ከተለመደው የዜና አሰራር ወጥቶ ሳቢ፣ ታሪክን መሰረት ያደረገ እና ዲጂታል አማራጮችን የተጠቀመ ሊሆን እንደሚገባ አብራርተዋል።
አዲስ የተመሰረተው የሚዲያ ፎረም እስካሁን በዘርፉ በዘልማድ ከሚታየውና ለአንድ ወቅት ብቻ ከሚደረግ የመረጃ ልውውጥ ባለፈ፣ በክልሎችና በሚዲያ ተቋማት መካከል ወጥነት ያለውና ቀጣይነት ያለው የመረጃ ቅብብሎሽ ስርዓት በመዘርጋት ለቱሪዝም እድገት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ታምኖበታል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ



Source: GetuTemesgen









No comments yet.