#Ethiopia | በጀርመን ሀምበርግ በተካሄደው የ2026ቱ የሃምበርግ ዘላቂ ልማት ኮንፈረንስ ላይ ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት ተሳታፊ የሆኑት ወ/ሮ ቤዛ በሻህ ኃይሌ፣ በነርቭ ዘንግ አፈጣጠር ችግሮች መከላከልና በእናቶችና ሕፃናት ጤና ዙሪያ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት እንዲሰጥ ጠንካራ ጥሪ አቀረቡ።
የሆፕ ስፓይና ቢፊዳ እና ሃይድሮሴፋለስ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ቤዛ፣ ከተለያዩ የፖለቲካ፣ የሳይንስ እና የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች ጋር አዳዲስ አጋርነቶችን ለመፍጠር በተዘጋጀው በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ የሀገራቸውንና የአህጉራቸውን ድምፅ በጉልህ አሰምተዋል።
ከጀርመን የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ፌዴራል ሚኒስትር ወ/ሮ ሬም አላባሊ-ራዶቫን በመቀጠል በዕለቱ ዋና ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ ቤዛ፣ በሕይወት የመጀመሪያዎቹ 1,000 ቀናት ውስጥ የተመጣጠነ ምግብን ለማረጋገጥ የሚደረግ ኢንቨስትመንት የእናቶችንና የሕጻናትን ጤና ለማሻሻል ወሳኝ ስትራቴጂ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
”ከእያንዳንዱ የምግብ እጥረት አኃዛዊ መረጃ ጀርባ የሚሰቃዩ ሕፃናት እና ቤተሰቦች መኖራቸውን ማስታወስ ይገባል” ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጇ፣ “የተደበቀ ረሃብ” በመባል የሚታወቀው የንጥረ-ነገር እጥረት በእናቶች እና በሕፃናት ላይ የሚያደርሰውን ዘላቂና ከባድ ተጽዕኖ በዝርዝር አስረድተዋል።
ይህ ችግር ግለሰቦችን ከመጉዳት ባለፈ ለሰው ልጅ ካፒታል፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ትልቅ እንቅፋት መሆኑን በማብራራት፣ በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ የሚደረግ መዋዕለ ንዋይ የትምህርት ጥራትና የኢኮኖሚ ምርታማነት መሠረት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመቅረፍ ድርጅታቸው ሆፕ ኤስ.ቢ.ኤች ላለፉት 10 ዓመታት በትኩረት የሰራባቸውን መፍትሄዎች ያጋሩት ወ/ሮ ቤዛ፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ያስመዘገበውን ጨውን በአዮዲን እና በፎሊክ አሲድ በጋራ የማበልጸግ ሂደት በልዩ አርአያነት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ አሳይተዋል።
ይህ በሀገር በቀል ጥናትና ምርምር የታገዘ ብሔራዊ የፖሊሲ ስኬት ሊመዘገብ የቻለው የመንግሥት ተቋማት፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍ እና የሲቪል ማኅበረሰብ በቅንጅት በመስራታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በመጨረሻም የሃምበርግ ዘላቂ ልማት ኮንፈረንስ እንደሚያንፀባርቀው ሁሉ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከአጠቃላይ የፖሊሲ ውይይቶች ባለፈ ተጨባጭና ዘላቂ ውጤት ወደሚያመጡ ተግባራዊ አጋርነቶች እንዲሸጋገር ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ



Source: GetuTemesgen









No comments yet.