የ40 ሀገራት አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ላሊበላ ከተማ ገቡ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ከአርባ በላይ ሀገራት እና ከአሥር በላይ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተወከሉ ዲፕሎማቶች ታሪካዊቷን የላሊበላ ከተማና ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጎብኘት ላሊበላ ገቡ።

የዲፕሎማቲክ ልዑካን ቡድኑ ላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ደማቅ ባህላዊ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

ጉዞው በቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ እና በኢትዮጵያ የዩኔስኮ ላይያዘን ኦፊስ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሪታ ቢሱናት የተመራ ነው።

ይህ ከፍተኛ የዲፕሎማቶች ልዑክ በቆይታው ከ800 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩትን፣ የሕንጻ ጥበብ እና የኢንጂነሪንግ ጥበብ ማስተርፒስ እንዲሁም የሃይማኖትና የታሪክ ሕያው ምስክር የሆኑትን የዓለም ቅርስ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ይጎበኛል።

የዲፕሎማቶቹ ጉብኝት የተከናወነው ላሊበላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት በተጓዙ አካላት በተደረገ ጥናት እና በዩሮኒውስ በተዘገበው መረጃ መሠረት፣ በዓለም ካሉ የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዳረሻዎች መካከል ቀዳሚ ከሆኑ አምስት ምርጥ ስፍራዎች አንዷ ተብላ በተመረጠችበት ወቅት መሆኑ ለጉብኝቱ ልዩ ትርጉም ሰጥቶታል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር እንዳመለከተው፣ ይህ ዓለም አቀፍ ዕውቅና የኢትዮጵያን የጥንታዊ ሥልጣኔ እና የባህል ውርስ ማረጋገጫ ከመሆኑም በላይ ሀገራችን በባህላዊ ቱሪዝም ያላትን ቀዳሚ መዳረሻነት በይበልጥ ያጠናክራል።

የልዑካን ቡድኑ በቆይታው የቅርሶቹን ድንቅ የታሪክ እና የጥበብ ሥራዎች ከመመልከት ባለፈ፣ ከቤተክርስቲያን አባቶች እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የውይይት መድረክ ይኖረዋል።

በተጨማሪም ከ”ዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት” ተወካዮች እንዲሁም ከፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር በመሆን ቅርሶቹን ከተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለመጠበቅ እንዲሁም በዘላቂ ልማት ዙሪያ ሰፊ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በአሁኑ ወቅት መንግሥት የላሊበላን ቅርሶች ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የጥበቃ ሥራዎችን ከማጠናከር ባለፈ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን የማሻሻል ሥራ በስፋት እያከናወነ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ ጊዜ ቱሪዝም ጎብኝዎችን መሳብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ማንነት ማሳያ፣ ቅርሶቿን መጠበቂያና በባህልና በተፈጥሮ ጸጋዎቿ አማካኝነት ብልጽግናን መገንቢያ መሆኑን ማሳሰባቸው ይታወሳል።

መንግሥት ዘርፉን ቁልፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጭ አድርጎ በወሰደው መሠረት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ አዳዲስ የቱሪዝም ኮሪደሮችና መዳረሻዎች በስፋት እየለሙ ይገኛሉ።

በዚህም ሳቢያ በዘንድሮው ዓመት ብቻ እስካሁን 1.4 ሚሊዮን ያህል ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውንና ይህም ለዘርፉ ማደግ ትልቅ ማሳያ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ የዲፕሎማቶች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ታሪካዊ ጉብኝት የላሊበላን ቅርሶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በበለጠ ለማስተዋወቅ፣ የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት እና የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ለማነቃቃት ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑ ተጠቁሟል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu

#Ethiopia #EBC #Lalibela #UNESCO #TourismEthiopia #LandOfOrigins #DiplomaticTour #HeritageConservation






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: