የሚከራይ የባንክ ሂሳብ ቁጥር

- Advertisement -
Sidebar AD

📌የባንክ ሂሳብ ቁጥርን በመሸጥና በማከራየት የሚፈጸም የማጭበርበር ወንጀል መበራከቱን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተናገረ

#Ethiopia | አጭበርባሪዎች የሌሎችን ሰዎች የባንክ አካውንት (የሂሳብ ቁጥር) በመግዛት እና በመከራየት፣ በወንጀል የተገኘን ህገወጥ ገንዘብ ለማዘዋወር እየተጠቀሙበት እንደሆነ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል።

ወንጀለኞቹ አብዛኛውን ጊዜ የባንክ አካውንት የሚገዙት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ሰዎች ወይም ከቅርብ ጓደኞቻቸው እንደሆነና ለዚህም የተወሰነ ገንዘብ እንደሚከፍሏቸው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ እጣወርቅ ተስፋዬ ነግረዉናል።

አጭበርባሪዎቹ በሌላ ሰው ስም የተከፈተ አካውንት የሚፈልጉበት ዋና ምክንያት፣ ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለመደበቅ እና በወንጀል ያገኙትን ገንዘብ ያለ ስጋት እንደልብ ለማዘዋወር ነው ያሉት ሀላፊዋ ለዚህም ተግባራቸው በአብዛኛው የንግድ ባንክ አካውንቶችን ይመርጣሉ ብለዋል።

ወንጀለኞቹ አካውንቱን እስከ 5,000 ብር በሚደርስ ክፍያ ከገዙ በኋላ፣ አዲስ ስልክ በመግዛት የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ (App) ያስጭናሉ። በመቀጠልም የባንክ አካውንቱን ባለቤት የይለፍ ቃል ( #Password ) በመቀበል፣ ሙሉ የአካውንት የማስተላለፍና የመቆጣጠር ስልጣኑን በእጃቸው እንደሚያስገቡ ምክትል ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።

“ከጓደኛዬ ወይም ከቤተሰቤ የመጣ ነው፤ በአንተ አካውንት ገቢ ይደረግና እኔ ለምነግርህ ሰው አስተላልፍ፣ የተወሰነውን ደግሞ አንተ ያዘው” በሚል ሰበብ በወንጀል የተገኘን ገንዘብ በሌላ ሰው አካውንት እንዲተላለፍ በማድረግ ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማሸሽ የሚፈልጉ አጭበርባሪዎች ቁጥር ስለመጨመሩም ተነግሯል።

ነገር ግን አንድ ሰው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የባንክ አካውንቱን ለሌላ አካል አሳልፎ ሰጥቶ፣ በአካውንቱ ላይ በወንጀል የተገኘ ህገወጥ ገንዘብ ከተዘዋወረና ይህ በምርመራ ከተረጋገጠ፣ በህግ ተጠያቂ የሚሆነው አካውንቱ በስሙ የተከፈተው ባለቤት እንደሆነ ተጠቁሟል።

“ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም” ያሉት ምክትል ዳይሬክተሯ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለአንድ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ከ1,550 እስከ 5,000 ብር ክፍያ በመቀበል የሂሳብ ቁጥራቸውን አሳልፈው የሚሰጡ በዝተዋል ብለዋል።

በዚህ መንገድ ሰዎች እስከ 25 ዓመት በሚደርስ እስራት በሚያስቀጣ የወንጀል ድርጊት እየተሳተፉ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው ሲሉ ምክትል ዳይሬክተሯ አስጠንቅቀዋል።

ዘገባው የሸገር ኤፍ ኤም ነው።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1