የነቢይ መኮንን የጥበብ በረከቶች

- Advertisement -
Sidebar AD

—-
አፈንዲ ሙተቂ
—-
ተወዳጁ ጋዜጠኛ፣ ገጣሚ እና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን ያረፈው የዛሬ ሁለት ዓመት በዚህ ቀን ነበር። ነቢይ በሕይወት ሳለ የሰራቸው የጽሑፍና የጥበብ በረከቶች የትኞቹ ናቸው? ባዮግራፊው በትክክል ስላልተጻፈ ሁሉንም ማስፈር ይከብዳል። ሆኖም የሚከተሉትን አስታውሳለሁ።
——
1. “ነገም ሌላ ቀን ነው”

በአሜሪካዊቷ ደራሲ ማርጋሬት ሚቸል የተጻፈውን “Gone with the Wind” የተሰኘ ታላቅ ድርሰት በአማርኛ ቋንቋ የተረጎመበት ድንቅ መጽሐፍ ነው። ይሁንና ነቢይ ያሳተመው የመጽሐፉን የመጀመሪያ ክፍል ብቻ ነው። ሁለተኛውን ክፍል ስለማሳተሙ መረጃው የለኝም። ነቢይ መጽሐፉን የተረጎመው ለአስር ዓመታት ያህል በማዕከላዊ እና በከርቸሌ በታሰረበት ዘመን በሲጃራ ፓኮዎችና በብጥስጣሽ ወረቀቶች ላይ እየጻፈ ነው።
——
2. “ናትናኤል ጠቢቡ”

ጀርመናዊው ጸሐፊ ተውኔት Gotthold Ephraim Lessing የጻፈውን “Nathan der Weise” የተሰኘ ቴአትር ወደ አማርኛ የተረጎመበት ርእስ ነው። ቴአትሩ በብዙ የዓለም ሀገሮች “Natahn the Wise” በሚለው የእንግሊዝኛ ስሙ ነው የሚታወቀው። በተውኔት ታሪክ በብዙ ቋንቋዎች ከተተረጎሙት ምርጥ ቴአትሮችም አንዱ ነው።

ነቢይ የተረጎመው ተውኔት በብሄራዊ ቴአትር ይታይ ነበር። ቴአትሩ በሙስሊሞች፣ በአይሁዶች እና በክርስቲያኖች መካከል የሀይማኖት መቻቻል እንዲኖር ነው የሚያስተምረው።
——
3. “ባለ ጉዳይ”

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተደጋግሞ የታየ Satirical ድራማ ነው። ድራማው በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ የሰፈነውን የጠነዛ ቢሮክራሲ እና የጉቦ አሰራር በአስቂኝ መንገድ የሚያሳይ ነው። የድራማው ዋና ገጸ-ባሕሪ “ቀናው ተበጀ” ይባላል። እርሱን ሆኖ የሰራው አክተር ደግሞ ፍቃዱ ተክለማሪያም ነው። በዚህም የተነሳ ፈቃዱ በድራማው ውስጥ የተጠራበት ስም “ቀናው ተበጀ” ቅጽል ስሙ ሆኖ ነበር።
—–
4. “ማፍቀር ነው መሰልጠን”

HIV- AIDS የሀገር አደጋ በሆነበት ዘመን ነቢይ መኮንን “ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩትን ማግለል በሽታውን ያባብሳል። ስለዚህ ፍቅር እንስጣቸው። አናግልላቸው” የሚል መልእክት ያለው ግጥም ገጥሞ የዘመኑ ወጣት ዘፋኞች እንዲዘፍኑት አድርጎአል። የዘፈኑ መጠሪያ “ማፍቀር ነው መሰልጠን” ሲሆን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ ይታይ ነበር።

ታዲያ ባላወቅኩት ሁኔታ ብዙዎች ግጥሙን የጻፈው ነቢይ መኮንን መሆኑን ሳይገልጹ ስራውን ሙሉ በሙሉ በዜማ ደራሲው አርቲስት ሚካኤል በላይነህ ስም ያወሱታል። ይህ ስሕተት መታረም አለበት።
—–
5. ስውር ስፌት

ነቢያ የገጠማቸውን ግጥሞች ያሰባሰበበት ባለ ሁለት ክፍል መድብል ነው። በዚያ መድብል ከሰፈሩት ግጥሞች መካከል ይህኛው ግሩም ነው።

ይቺው ናት ኢትዮጵያ…
ይቺው ናት ዓለምህ፣
ብቻዋን የተኛች ከዓለም ተደብቃ!!
አኪሯ ቀዝቅዞ፣
“ያንቀላፋች ውቢት” ያንተው የክት እቃ…
ምን ትሆን እንግዲህ ሀገርህ ናት እሷ!
ልቧን አታውልቃት አትጨቅጭቃት በቃ፣
አብረህ አንቀላፋ፣ ወይ አብረሃት ንቃ!!
(ነብይ መኮንን፡ “ስውር-ስፌት”)
——-
6. “የኛ ሰው በአሜሪካ”

ነቢይ መኮንን አሜሪካ በሄደበት ጊዜ በዚያ ስለሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን የጻፈው አስገራሚ፣ አስቂኝ እና አስተማሪ የጉዞ ማስታወሻ ነው። ማስታወሻው መጀመሪያ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ከቀረበ በኋላ በ1997 ገደማ በአንድ መጽሐፍ ታትሞ ወጥቷል።
——-
7. “የዳቪንቺ ኮድ”

ነቢይ በ1999-2000 ዳን ብራውን የጻፈውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ የነበረውን “The Davinci Code” የተሰኘ መጽሐፍ ወደ አማርኛ ተርጉሞ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በተከታታይ ያስነብብ ነበር። እኛም ትርጉሙን በአንድ መጽሐፍ እንዲያሳትም ነግረነዋል። ይሁንና መጽሐፉ የታተመ አይመስለኝም።
——–
8. “ነገር የገባት ሰጎን”

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ1995 በፓሪስ ከተማ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለሀገሯ የወርቅ ሜዳሊያ ስታስገኝ በመላው ሕዝባችን ስሜት ላይ ከፍተኛ ደስታ ነው የፈጠረችው። ነቢይ መኮንንም ደስታው ፍንቅል ብሎ ወጥቶ ለጥሩነሽ ያለውን አድናቆት “ነገር የገባት ሰጎን” በሚል ግጥም ገልጾላታል። ግጥሙም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ወጥቶ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

ጥሩነሽ ከአምስት ዓመታት በኋላ በቤጂንግ ኦሊምፒክ ለሀገሯ የወርቅ ሜዳሊያ ስታስገኝ ነቢይ ስሜቱን የገለጸበትን “ነገር የገባት ሰጎን- ቁጥር ሁለት” የሚል ርእስ ያለው ግጥም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ አስነብቦናል።
——
የነቢይን የስነ-ጽሑፍ እና የኪነ-ጥበብ ውሎች በጥቂቱ እንዲህ ቃኝቻለሁ። ከኔ የተሻለ መረጃ ያላችሁ ወዳጆቻችን የምታውቁትን ልትጨምሩበት ትችላላችሁ።

Dear Nebiy,
You were a gifted literary figure and an iconic scholar. We miss you so much. May your soul rest in peace.
—–
አፈንዲ ሙተቂ
ሰኔ 26/2017


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1