‎የጭጋግ ሰማይ ስር ትዝታዎች

- Advertisement -
Sidebar AD


‎#Ethiopia | ​ከአዝማሪው ክራር ቅኝት ይበልጥ በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ጥልቅ ስሜት የሚቀሰቅሰው የሰኔ ማብቂያ ነፋስ ይመስለኛል። ሰኔ 26 ቀን ሲባት፣ ተፈጥሮ አረንጓዴ ካባዋን ለብሳ መስከረም 25 ላይ እስክትሰናበተን ድረስ ያለው ጊዜ ዝም ብሎ የአየር ንብረት ለውጥ ብቻ አይደለም፤ የናፍቆት፣ የፍቅር እና የትዝታ ወቅት እንጂ።

‎ክረምት ሲጠባ መጀመሪያ አእምሯችን ላይ ድቅን የሚለው በትምህርት ቤት መዘጋት የሚፈጠረው ያ ድንገተኛ ነጻነት ነው። ሰኔ 30 ውጤት ተቀብለን ወደ ቀጣይ ክፍል ለመሻገር ደብተሮች ተጠቅልለው የሆነ ስርቻ ውስጥ ሲቀመጡ የሚሰማው ደስታ መጀመሪያ ላይ የላቀ ቢሆንም፣ ቀናት እያለፉ ሲሄዱ ግን የትምህርት ቤት ጓደኞቻችን ናፍቆት ቀስ እያለ ልባችንን ማንኳኳት ይጀምራል።

‎ያኔ በየቀኑ አብረው የሚቦርቁ፣ የሚጣሉና የሚታረቁ የትምህርት ቤት ጓደኞች መለያየት በልጅነት ልብ ውስጥ ትልቅ ባዶነት ሲፈጥር፣ ያንን ናፍቆት ለመወጣት ደግሞ የሰፈሩ ጨዋታና በዝናብ ውስጥ መሯሯጥ ይጀመራል።

‎​ያ የደመና መጥቆርና መክበድ ግን የዝናብ ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ ፍቅር መሰብሰቢያ ምልክትም ጭምር ነው። በብርዱ ወቅት የአመጋገብ ስርዓታችን እንኳ ሳይቀር ይቀየራል፤ በከሰል እሳት ላይ የበሰለ ድንችና የተጠበሰ በቆሎ እየተቆረጠመ፣ በጢሱ መዓዛ የታወደው ቤት ውስጥ የሚደረገው ጨዋታ የክረምቱን ቅዝቃዜ ያቅልጠዋል።

‎ይሁን እንጂ ክረምት በከተማውና በገጠሩ ያለው ገጽታ የተለያየና የየራሱ ጣዕም ያለው ነው። በከተማው ዝናብ ድንገት ሲያካፋ የሚታየው ትርምስና ሩጫ ለየት ያለ ድራማ አለው። ጃንጥላ ለመዘርጋት የሚደረገው ጥረት፣ መጠለያ ፍለጋ በረንዳ ስር መሻማት፣ እና መንገዶች በጎርፍ ተሞልተው መኪናዎች እግረኛውን በጎርፍ ሲረጩ የሚፈጠረው የቁጣና የግርምት ስሜት የከተማው የክረምት መገለጫዎች ናቸው።

‎በገጠሩ ግን ነገሩ ሌላ ነው፤ እዚያ የስራው ጫና የበረታና ብዙ ነገር የሚከወንበት ነው። እረኛው ህጻን በገሳ ተጠቅልሎ፣ ዝናቡና ብርዱ እየገረፈው ከብቶቹን የሚጠብቅበት ያ ምስል የጽናትንና የገጠሩን ህይወት ትግል ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

‎​ምሽት ላይ ግን ተፈጥሮ ሁሉንም ጸጥታ ታለብሰዋለች። ማታ ሰው ሁሉ ወደየቤቱ ገብቶ፣ መብራት ጠፍቶ፣ በጨለማው ውስጥ በቆርቆሮው ላይ የሚዘንበው የዝናብ ድምፅ የሚፈጥረው ዜማ ወደ ጥልቅ እንቅልፍና ህልም የሚወስድ አስማታዊ ኃይል አለው።

‎ይህ የዝናብ ወቅት በመንፈሳዊና በባህላዊ በዓላትም የተከበበ ነው። ነሐሴ ሲጠባ የ16ቱ ቀን የፍልሰታ ጾም ሰሞን ሌሊቱ በማህሌትና በሰዓታት ይደምቃል። ሌሊቱን ሙሉ ሲያገለግሉ አድረው ነጋት ላይ በኪዳን፣ ቀን በቅዳሴ ለመቁረብ ህጻናቱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተያይዘው በብርዱ ቆመው ረጅሙን ወረፋ የሚጠብቁበት ያ መንፈሳዊ ትጋት በልጅነት ትዝታችን ውስጥ የማይረሳ አሻራ ጥሎ ያልፋል።

‎​ክረምቱ እየገፋ ሲሄድ ደግሞ ደብረታቦር (ቡሄ) መጥቶ ሰፈሩ በህጻናት የሆያሆዬ ጭፈራና በጅራፍ ድምጽ ይናወጣል። በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ ልጃገረዶቹም በበኩላቸው የአሸንዳ፣ አሸንድዬ እና የባህላዊው ሶለል ጭፈራቸውን ይዘው አደባባዩን በውበትና በደስታ ይሞሉታል።

‎በመጨረሻም የክረምቱን ማብቂያና የአዲስ ዘመን መባቻን ለማብሰር በጳጉሜ ወራት የሚወሰደው የጸበል ጥምቀት አካልን ብቻ ሳይሆን ነፍስን ጭምር አጥቦ ለአዲሱ ብርሃን ያዘጋጃል።

‎ክረምት አልፎ መስከረም ሲጠባ፣ ምድሪቱ አረንጓዴዋን አውልቃ በጫጫታና በአደይ አበባ ስትደምቅ፣ እኛ ግን ከዝናቡ ጋር አብረን ያሳለፍነውን ያንን ድንቅ ትዝታ በልባችን ይዘን እንቀጥላለን።


‎​እናንተስ ምን ትዝታ አላችሁ?

‎ጌትነት ተመስገን
‎Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

‎#getutemesgen #getu #ጌጡ


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1