ዘምዘም ባንክ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ የአክሲዮን ምዝገባ ፈቃድ አገኘ!

- Advertisement -
Sidebar AD

#Fastmereja I ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ ተቋም በመሆን የሚታወቀው ዘምዘም ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን (ECMA) ይፋዊ የአክሲዮን ምዝገባ ማፅደቂያ ማግኘቱን አስታወቀ።

ባንኩ ከግብይት አማካሪው ወጋገን ኢንቨስትመንት ባንክ ጋር በመሆን በሰጠው የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሰነደ ሙዓለ‐ንዋይን ለሕዝብ የማቅረብ እና የግብይት መመሪያ ቁጥር 1030/2024 መሠረት ምዝገባው በይፋ መጽደቁን ይፋ አድርጓል።

ይህ ዕውቅና ተቋሙ በኢትዮጵያ አዲስ ለተጀመረው የካፒታል ገበያ ታሪክ የመጀመሪያውን የአክሲዮን ምዝገባ ፈቃድ የወሰደ ቀዳሚ ባንክ የሚያደርገዉ ሲሆን ይህ ፈቃድ ተቋሙ ነባር አክሲዮኖቹን በሕጋዊ መንገድ እንዲመዘግብና አዳዲስ አክሲዮኖችን ለሕዝብ በማቅረብ ካፒታሉን በቀልጣፋ መንገድ እንዲያሳድግ ዕድል እንደሚፈጥርለት ተገልጿል።

የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ መሊካ በድሪ እንደገለፁት፤ በጸደቀው የምዝገባ መግለጫ መሠረት ተቋሙ ያሉትን ነባር 5 ሚሊዮን አክሲዮኖች ያስመዘገበ ሲሆን፣ በተጨማሪም በትርፍ ድርሻ ወደ ካፒታል የሚቀየር 1 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 1 ሚሊዮን አዳዲስ አክሲዮኖችን ይፋ ማድረጉን ገልፀዉ በጥቅሉ አጠቃላይ ካፒታሉን ወደ 15 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ማቀዱንም ጨምረው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል ወይዘሮ ራሄል ካሳ በበኩላቸዉ፤ ይህ ስኬት በሀገሪቱ አዲስ ለተጀመረው የካፒታል ገበያ መዳበር እና ከወለድ ነፃ ለሆነው የባንክ ኢንዱስትሪ መስፋፋት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ሲሉ ገልፀዋል።

ባንኩ ካፒታሉን ከማሳደጉ ባሻገር፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም የፋይናንስ መለኪያዎች ላይ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቡ ተጠቁሟል። በዚህም መሠረት አጠቃላይ ገቢው የ36% ዕድገት በማሳየት 3 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የተጣራ ትርፉ ደግሞ የ35% ጭማሪ በማሳየት 1.8 ቢሊዮን ብር ሆኗል። እንዲሁም የፋይናንስ ጥንካሬውን በሚያሳይ መልኩ የተከፈለ ካፒታሉ (Paid-up Capital) ከፍተኛ እምርታ በማሳየት ከ2.65 ቢሊዮን ብር ወደ 5.64 ቢሊዮን ብር ማደጉ ነዉ የተገለፀዉ።

በሌላ በኩል፣ በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለውን እምነት በሚያሳይ መልኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ በ81% በማደግ 21 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ ደግሞ 29.1 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል።

ባንኩ ለቴክኖሎጂ በሰጠው ልዩ ትኩረት ባስተዋወቀው “አንሳር ዲጂታል” የተሰኘ የፋይናንስ አገልግሎት፣ በአጭርጊዜ ውስጥ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የፋይናንስ አቅርቦትን ለ9,800 በላይ ደንበኞች ማድረስ ችሏል።

#ቢዝነስ ዘገባ






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1