በሽብር ወንጀል የተከሰሱት እነ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና 52 ተከሳሾች የተከሰሱበትን ክስ ይከላከሉ ወይስ በነጻ ይሰናበቱ የሚ

- Advertisement -
Sidebar AD

በሽብር ወንጀል የተከሰሱት እነ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና 52 ተከሳሾች የተከሰሱበትን ክስ ይከላከሉ ወይስ በነጻ ይሰናበቱ የሚለው ጉዳይ ላይ ብይን ሳይሰጥበት በድጋሚ ተራዘመ።

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የቀድሞ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው እንዲሁም ዶ/ር ካሳ ተሻገር፣ ዶ/ር ጫኔ ከበደን ጨምሮ በድምሩ 52 ተከሳሾች የፍርድ ውሳኔ ሳያገኙ ላለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ በእስር ላይ ይገኛሉ።

ክሱ የተመሠረተው መጋቢት 2016 ዓ.ም ሲሆን፣ ጉዳዩ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሕገ መንግሥትና ፀረ-ሽብር ወንጀሎች ችሎት እየታየ ይገኛል።

ተከሳሾቹ በተለያዩ ወቅቶች ካለባቸው የጤና ችግር ጋር በተያያዘ፣ ከቤተሰብ ጥየቃ፣ ከሰብአዊ መብት ሁኔታ፣ እና ሌሎችም ደረሰብን በማለት በሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች ዙሪያ ችሎቱ የተለያዩ ቀጠሮዎችን በመስጠት ጉዳያቸውን ሲመለከት የቆየ በመሆኑ የተከሰሱበትን ዋናው የክስ መዝገብን የማየት ሂደት በተለዋጭ ቀጠሮዎች ከ 4 ጊዜ በላይ ሲራዘም ቆይቷል።

በዋናው የሽብር ክስ መዝገብ ላይ ብይን ለመስጠት ቀደም ሲል ለሐምሌ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ችሎቱ ጉዳዩን በተጨማሪ ዝግጅት አጠቃሎ ለማቅረብ ለዛሬ ሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ለተለዋጭ ቀጠሮ አስተላልፎት ነበር።

ችሎቱ ዛሬ የሚሰጠው ብይን ተከሳሾቹ የተከሰሱበትን ክስ ይከላከሉ ወይስ የነጻ ይሰናበቱ የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ እንደሚሆን ቢጠበቅም በድጋሚ በተለዋጭ ቀጠሮ ለ ጥቅምት 6/2019 ዓም በመስጠት ውሳኔውን አራዝሞታል።

ፍርድ ቤቱ ብይኑን ማጠናቀቁን ገልጾ ነበር፤ ይሁን እንጂ የተወሰኑ ተከሳሾች በችሎት ባለመገኘታቸው ብይኑን ለንባብ ማቅረብ እንደማይችል በመግለጽ ንባቡን አላደረገም።

በዛሬው ችሎት ፍርድ ቤቱ ያሰማዋል ተብሎ ሲጠበቅ ከነበረው ብይን በተጨማሪ ከተከሳሾቹ አንዱ ከሆኑት ከዶ/ር ካሳ ተሻገር እና ከጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ስልክ ቁጥር ጋር በተያያዘ ቁጥራቸውን ሌላ ሰው እየተጠቀመበት መሆኑን በመግለጽ ከእዚህ ቀደም በችሎቱ ያቀረቡትን ቅሬታ በተመለከተ ኢትዮ ቴሌኮም ለችሎቱ ይሰጠዋል ተብሎ የሚጠበቀውን ምላሽ የመስማት ጉዳይ ነበር።

ከዶ/ር ካሳ ተሻገር እና ከጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ስልክ ቁጥሮች ጋር በተያያዘ ኢትዮ ቴሌኮም የላከውን ምላሽ ችሎቱ በንባብ አሰምቶታል።

በምላሹ መሠረት፣ የሁለቱ ተከሳሾች ስልክ ቁጥሮች ለረዥም ጊዜ ከአገልግሎት ውጭ በመቆየታቸው በኩባንያው አሠራር መሠረት ጊዜው አልፎበት (expire አድርጎ) ለሌሎች አዳዲስ ተጠቃሚዎች መዘዋወራቸውን ኢትዮ ቴሌኮም አረጋግጧል።

በዋናው ጉዳይ ላይ የሚጠበቀው ብይን ተከሳሾቹ አቃቤ ሕግ ባቀረበባቸው ማስረጃ ላይ ተመስርተው ክሱን ሊከላከሉ ይገባል ወይስ አቃቤ ሕግ ክሱን በበቂ ማስረጃ ስላላስረዳ በነጻ ሊሰናበቱ ይገባል የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ነው።

የተከሳሾች ጠበቃ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል “ተከሳሾቹ ከእዚህ ቀደም በችሎት ውሎዎች ላይ አቃቤ ሕግ ካቀረባቸው የድምጽ፣ የጽሑፍ እና የፎረንሲክ ማስረጃዎች ጋር በተያያዘ አስተያየታቸውን ማቅረባቸውን”ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ይህን አስተያየት እና አቃቤ ሕግ ያቀረበውን ማስረጃ መርምሮ፣ ማስረጃው ክሱን በበቂ ሁኔታ የሚያስረዳ ሆኖ ካገኘው ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ፣ ካላገኘውም ተከሳሾቹ ያለ ተጨማሪ ክርክር በነጻ እንዲሰናበቱ ብይን የሚሰጥበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቅ ነበር ብለውናል።

ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ሙሉ ተገኝነት መሠረት በማድረግ ብይኑን ወደ ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱን ዘግቷል።

የበጀት ዓመቱ መጠናቀቁን ተከትሎ የዳኝነት አገልግሎት ክብደትና ውስብስብነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የፌዴራል የመጀመሪያ፣ ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በየአመቱ ከነሐሴ 1 እስከ መስከረም 30 ለ2 ወራት በከፊል ዝግ ሆነው የሚቆዩ መሆኑ ይታወቃል።

@tikvahethiopia




Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: