«የጥላቻ ንግግር ፍጻሜ፦ ዛሬ በስሜት የተነገረ ቃል ነገ ዘብጥያ ያወርዳል!»

- Advertisement -
Sidebar AD

ከአስቴር በዳኔ ንግግር በመነሳት የተዘጋጀ

በቅርቡ አርቲስት አስቴር በዳኔ የተወሰኑ ማህበረሰቦችን በጅምላ በመፈረጅ እና በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት «የበቀል እርምጃ» አስመስላ በማቅረብ የተናገረችው ንግግር በማህበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ ቅሬታን አስነስቷል።

ብዙዎች የሚናገሩት አደገኛ ቃል በጊዜ ሂደት የታሪክ እና የሕግ ተጠያቂነት ያስከትላል ወይንስ እንዲሁ አየር ላይ በኖ ይቀራል በሚል ሲጠይቁ ይደመጣል።

የዓለም አቀፍ የፍትሕ ታሪክ የሚያሳየን ግን የጥላቻ ንግግሮች የትም ያህል ጊዜ ቢወስዱ የሕግ ተጠያቂነት ማስከተላቸው እንደማይቀር ነው ዛሬ በችኮላ ወይም በስሜት የሚነገሩ የሚያጋጩ ቃላት ነገ ፍትሕ በሚነግስበት ጊዜ ዘብጥያ የሚያወርዱ የሕግ ማስረጃዎች ሆነው ይመዘገባሉ።
የጥላቻ ንግግር በተለይም ታዋቂ ሰዎች ወይም የህዝብ ልሳኖች የሚያሰራጩት ሲሆን በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለሚደርስ የጅምላ ጥቃት ማበራቻ እንደሚሆን በታሪክ በተደጋጋሚ ታይቷል።

የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶችም ይህንን በግልጽ እንደ ወንጀል ፈርጀው እርምጃ ወስደዋል። እ.ኤ.አ በ1994 በሩዋንዳ ከተከሰተው አሰቃቂ የጅምላ ጨፍጨፋ በኋላ የሩዋንዳ ዓለም አቀፍ ወንጀል ትሪቡናል (ICTR) በታዋቂው የ«Media Trial» ውሳኔው መሳሪያ አንስተው የተዋጉትን ብቻ ሳይሆን በሬዲዮ እና በጋዜጣ የጥላቻ ንግግር እና የጥቃት ጥሪ ያቀረቡ የህዝብ ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች ለፍርድ አቅርቧል።

በዚሁ መዝገብ የRTLM ሬዲዮ ጣቢያ መስራች የነበረው ፈርዲናንድ ናሂማና እና ጋዜጠኛ ሀሰን ንጌዜ በቀጥታ ሰውን ባይገድሉም በቃላቶቻቸው ጥላቻን በመዝራታቸው እና ጥቃትን በማበራታታቸው በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የጽኑ እስራት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በተካሄደው የኑረምበርግ ፍርድ ቤት (Nuremberg Trials)፣ «ደስ ስቱርመር» በተባለው ጋዜጣ የናዚን የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ያሰራጭ የነበረው ጁሊየስ ሺራይቸር፣ በቀጥታ የጦር መሳሪያ ባያነሳም በቃላቱ ባሰራጨው አደገኛ ጥላቻ ምክንያት በሰው ልጅ ላይ ወንጀል በመፈጸሙ ለፍርድ ውሏል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ከዩጎዝላቪያ መፍረስ በኋላ በተቋቋመው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት (ICTY) የፖለቲከኞች እና የብዙኃን መገናኛ ሰዎች አጋጫኝ ንግግሮች በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተደርገው ተወስደው ለዓመታት ተከታትለው ለፍትሕ እንዲቀርቡ ተደርገዋል።

አርቲስት አስቴር በዳኔ «አማራ እና ኦርቶዶክስ የሀገር ባለቤት ነኝ ብሎ ተቀምጧል፤ ቶለሬት የማያደርግ ትውልድ ተነስቶ እየተበቀላቸው ነው» ስትል ያደረገችው ንግግር በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርስን ጥቃት እንደ «በቀል» አድርጎ በማቅረብ ወንጀልን የማበረታታት ይዘት ያለው በመሆኑ በዲጂታል ዘመን ማናቸውም የማህበራዊ ሚዲያ ንግግሮች እና መረጃዎች በቀላሉ የማይጠፉ የታሪክ ሰነዶች ናቸው።

ፍትሕ እና የሕግ የበላይነት ሙሉ በሙሉ በሚሰፍንበት ጊዜ እነዚህ ንግግሮች ማህበረሰብን ለጥቃት አጋልጠዋል በሚል በሕግ ፊት የመጠየቂያ ማስረጃዎች መሆናቸው አይቀሬ ነው።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ማንኛውም ዜጋ ወይም ማህበረሰብ «የሀገሬ ባለቤት ነኝ» ብሎ ማሰቡና መናገሩ ህገ-መንግስታዊ እና ዜጋዊ መብቱ እንጂ በፍጹም ወንጀል ሊሆን አይችልም።

ይህንን ዜጋዊ መብት እንደ «የበላይነት ጥያቄ» አድርጎ በመተርጎም፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ግፍና ጥቃት እንደ «ተገቢ የበቀል እርምጃ» አድርጎ ማቅረብ ግን ነገ ምንይዞ እንደሚመጣ ታሪክ ይፈርዳል

በቃላት የሚዘራ ጥላቻ በሰዎች ህይወት ላይ ጥፋት ያመጣል ዛሬ በስሜት ወይም በኃይል አሰላለፍ ተሸፍነው የሚያልፉ ይመስሉ እንጂ በሕግ እና በፍትሕ ስርዓት ውስጥ የጥላቻ ንግግሮች ጊዜ አይሽራቸውም።

አርቲስቶች እና ታዋቂ ሰዎች የሚናገሩት እያንዳንዱ ቃል ነገ በፍርድ ቤት እና በታሪክ ፊት እንደሚያስጠይቅ ተረድተው ከህዝብ አጋጫኝ ንግግሮች ሊቆጠቡ ይገባል።




Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: