በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ) የዋጋ ንረት ለማቃለል ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ዋጋ ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ፤ እንዲሁም በሐገር ውስጥ ለማምረት የሚያስፈልገው ጥሬ ዕቃ ቀረጥ እንዳይከፈልበት፣ ወይም አነስተኛ ታክስ እንዲጣልበት እንዲሁም በገጠር ለሚኖሩ ሴቶች እና ለአቅመ ደካማ ተማሪዎች ተደራሽ እንዲሆን፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን አስታወቋል።
ፌዴሬሽኑ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጾ፤ ባለሙያዎችን ያካተተ አደረጃጀት በመፍጠር ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ገነት ሥዩም እንዳገለጹት፤ ተቋማቸው በዋጋው ውድነት ዙሪያ በጋራ ለመስራት ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል። በተጨማሪም ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር እየሰራ እንደሆነ ተገልጿል።
በሚካሄዱ አገራዊ መድረኮች ላይም ችግሩን በማንሳት ሰፊ ውይይት እንዲካሄድበት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
በቀጣይ የምርት ጥራቱን ለማስጠበቅ እና የዋጋ ውድነቱን ለመቀነስ ሴቶች ሀገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች በቀላሉ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰሩ ተገልጿል።
ከውጪ የሚገቡ ምርቶችም በዝቅተኛ ታክስ የሚገቡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሰራበት ተመላክቷል።
ፌዴሬሽኑ በተለይም ሴት ተማሪዎች እና ወጣቶች በንጽህና መጠበቂያ እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይስተጓጎሉ ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ዋና ዳይሬክተሯ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ከውጪ የሚገባ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያን ከታክስ ነጻ በማድረግ በዝቅተኛ ዋጋ ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችለው እንቅስቃሴ በገንዘብ ሚኒስቴር እና በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀዳሚ አስተባባሪነት ቢጀመርም እስከ አሁን አልተተገበረም።
በስፍራሽ ደመላሽ
Source: Yeneta Tube








No comments yet.