#Ethiopia | የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሁለንተናዊ ሀገራዊ ለውጡን መነሻ በማድረግ ለበርካታ ዓመታት ሲተገብረው የቆየውን ተቋማዊ ሪፎርም በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥል አስታውቋል። በ2019 በጀት ዓመትም ሪፎርሙን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።
ኮርፖሬሽኑ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይትን በቢሾፍቱ ከተማ ለሁለት ቀናት ያካሄደ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ የታቀዱ ሥራዎችን 97 በመቶ ማሳካቱ ተገልጿል። በገቢ ዕድገት፣ በቤት ልማት፣ በአፈጻጸም አቅም እና በቤት አስተዳደር የተመዘገቡ ውጤቶችም የተቋሙን የለውጥ ጉዞ እንዳጠናከሩ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም የሕዝብና የመንግሥት ጥቅምን ለማስጠበቅ በተደረጉ የፍርድ ቤት ክርክሮች በርካታ ይዞታዎችን ማስመለስ መቻሉ ተገልጿል።
በውጭ ገበያ መስፋፋትን በተመለከተም፣ በደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ የቤት ልማት ፕሮጀክት ለማከናወን ከደቡብ ሱዳን ኢኳቶሪያል ስቴት ጋር የተደረሰውን ስምምነት ወደ ተግባር ለማስገባት ሥራዎች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
በፕሮጀክቶች ዘርፍ የፒያሳ እና የጎልድ ሳይት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ አገልግሎት መግባታቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ ዘመናዊ 3ዲ የግንባታ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት የመጀመሪያ የሙከራ ቤቶች ግንባታም በሂደት ላይ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም የቤቶች ቆጠራና የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ በመጠናቀቁ ዘመናዊ የቤት አስተዳደር ሥርዓት መጠናከሩን እና ከደንበኞች ጋር በትብብር የተገነቡ የንግድ ቤቶች ወደ ኪራይ አገልግሎት በመግባታቸው ከፍተኛ ገቢ ማስገኘት መጀመራቸው ተጠቁሟል።
ኮርፖሬሽኑ በ50ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓሉ ወቅት የተቋሙን የግማሽ ምዕተ ዓመት ታሪክና ስኬቶች የሚያሳዩ መርሃ ግብሮችን ለአራት ተከታታይ ቀናት በድምቀት ማካሄዱ ተገልጿል። ይህም የተቋሙን ገጽታ በአዎንታዊ መልኩ ለመቀየር አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተጠቅሷል።
በ2019 በጀት ዓመት የሚተገበሩ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ዘመናዊና ፈጣን የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ሥራ ላይ ማዋል፣ የቤት አቅርቦትን ለማሳደግ ሰፋፊ የቤት ልማት ፕሮግራሞችን መተግበር፣ የገቢ ምንጮችንና የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋፋት እንዲሁም የሰው ኃይልና የአሠራር አቅምን ማጠናከር መሆናቸው ተገልጿል።
ኮርፖሬሽኑም እነዚህን ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎች በመተግበር ለሀገራዊ የቤት ልማት ዕቅድ ስኬት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታውቋል።



Source: GetuTemesgen









No comments yet.