ዘመን ባንክ ከ10.2 ቢሊየን ብር በላይ ያልተጣራ ትርፍ አስመዘገበ፤ አጠቃላይ ሀብቱ 116 ቢሊየን ብር ደረሰ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ዘመን ባንክ በ2017/2018 (እ.አ.አ. 2025/26) የበጀት ዓመት 10.2 ቢሊየን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ። በዚሁ ዓመት የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 116 ቢሊየን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የፋይናንስ አፈጻጸሙም በበርካታ መለኪያዎች እድገት ማሳየቱ ተገልጿል።

ባንኩ ከሐምሌ 17 እስከ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው ዓመታዊ የማኔጅመንት ስብሰባ ላይ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ እንዬ ቢምር፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ ለስኬቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የማኔጅመንት አባላትና ሠራተኞች ምስጋና አቅርበዋል።

የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይና የሪቴል ባንኪንግ ቺፍ ኦፊሰር አቶ አስራት ታደሰ በበኩላቸው፣ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከ14 ቢሊየን ብር በላይ፣ አጠቃላይ ገቢ 17.8 ቢሊየን ብር እና ጠቅላላ ካፒታል 26 ቢሊየን ብር መድረሱን ገልጸው፣ የባንኩ አፈጻጸም በዘርፉ መለኪያዎች ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደነበር አስታውቀዋል።

በሪፖርቱ መሠረት፣ የደንበኞች ተቀማጭ ገንዘብ በ32 በመቶ አድጎ 85.4 ቢሊየን ብር ደርሷል። የውጭ ምንዛሬ ግኝት 698 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን፣ የተከማቸ ብድር 52.59 ቢሊየን ብር መድረሱም ተገልጿል። ባንኩ እነዚህ ውጤቶች ውጪያዊ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ያሳየውን ጠንካራ አቅም እንደሚያመለክቱ ገልጿል።

ባንኩ በማህበራዊ ሀላፊነት መርሃ ግብሮቹ ስር በአዲስ አበባ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የፋይናንስ እውቀት ማበልጸጊያ ስልጠናዎችን መስጠቱን ጠቅሶ፣ ህብረተሰቡን ከፋይናንስ ማጭበርበር ለመጠበቅ በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶችን ማስተላለፉንም አመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት ዘመን ባንክ 142 ቅርንጫፎችን በመላ ሀገሪቱ በማሰራጨት ለደንበኞቹ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጿል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1