የሐምሌ ቅዱስ ገብርኤልን በጂምናዚየም አከበርን

- Advertisement -
Sidebar AD

በአሜሪካ ሚኒሶታ የሚገኘው የብሥራተ ገብርኤል እና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በአስደንጋጭ የእሳት አደጋ ቢጎዳም፣ ጠንካራዎቹ የተዋሕዶ ልጆች ቅዱስ ቁርባን ከመቀበልና የሐምሌ ቅዱስ ገብርኤልን የንግሥ በዓል ከማክበር አልተገዱም።

ይህ አደጋ እጅግ አሳዛኝና ልብ የሚሰብር ነው። የቤተ ክርስቲያኑ ምዕመናን ከስምንት ዓመታት በላይ በኪራይ ቤተ ክርስቲያን እያመለኩ፣ ኪራይ ከፍለው፣ በትጋት ገንዘብ ቆጥበው፣ በኢትዮጵያም ችግር በተፈጠረ ቁጥር ድጋፋቸውን ሳያቋርጡ በመላክ በመጨረሻ በኖኅ መርከብ ቅርጽ የተሠራ ውብ ቤተ ክርስቲያን ገዙ።

የምርቃቱ ዕለት የነበረው ደስታ፣ የምስጋና ዝማሬ፣ ቅኔና ወረብ፣ የጳጳሳቱ፣ የካህናቱ፣ የዲያቆናቱና የምዕመናን ፊት ላይ የነበረው ፈገግታ እስካሁን አይረሳኝም።

ነገር ግን ያ ታላቅ ደስታ ሦስት ወራት እንኳ ሳይቆይ፣ ምክንያቱ እስካሁን ባልታወቀ ድንገተኛ የእሳት አደጋ ቤተ ክርስቲያኑ ተቃጠለ። ይህን ዜና ከአካባቢው ሚዲያ ስሰማ ሰውነቴ ተንቀጠቀጠ፤ “ለምን?” የሚል ጥያቄም ውስጤን አስጨነቀኝ። ሆኖም ሁሉም ነገር ለበጎ እንደሚሆን፣ እግዚአብሔርም ለሁሉ ምክንያት እንዳለው በማመን ራሴን አጽናናሁ።

ከሀገር ውጭ ለሚኖር ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ስፍራ ብቻ አይደለችም፤ ሀገር ናት፣ ቤተሰብ ናት፣ ዘመድ ናት፣ ጓደኛ ናት፣ መጽናኛም ናት። ስለዚህ እንዲህ ያለ አደጋ እነዚህን ሁሉ በአንድ ጊዜ እንደ ማጣት የሚሰማ ህመም ነው።

ሆኖም እምነታቸው ከሕንፃው በላይ መሆኑን አሳዩ። ቤተ ክርስቲያናቸው ቢቃጠልም፣ በሰፊ ጂምናዚየም ተሰብስበው ቅዱስ ቁርባን ተቀብለው፣ የሐምሌ ቅዱስ ገብርኤልን በዓል በክብር አከበሩ። ይህ የእምነት ጽናት እና የመንፈስ ብርታት ለሁላችንም ትልቅ ትምህርት ነው።

በመላው ዓለም የምንገኝ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ የሆንን ክርስቲያኖች፣ ለእነዚህ እምነተ ጠንካሮች ከጎናቸው መቆማችንን እናሳይ።

የድጋፍ (GoFundMe) ሊንክ
https://gofund.me/baf1038b6

“እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።”
— ሮሜ 8፥28






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: