በሆነ በዘመን የቀረውን እኔን የመለሰ አልበም!

- Advertisement -
Sidebar AD

የአህመድ ተሸመ (ዲንቢ) “ጊዜ አይሄድም”!

ተስፋዬ እሸቱ (ረ/ፕሮፌሰር)

#Ethiopia | መቸም የአህመድ ተሾመ (ዲንቢ) ድንቅ የዜማ ደራሲነት ሰብዕና ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ለራሱ የሠራቸውን ዘግየት እናድርግና ለሌሎች የሙያ አጋሮቹ ሠርቶላቸው በብዙኋን አድማጮች ዘንድ ሰፊ ተቀባይነትን ያገኙትን የዜማ ድርሰቶቹን እንዘርዝር ብንል ጊዜም ሥፍራም አይበቃንም፡፡

እንደው ከግምታችን በላይ ስለሆነው ስለዲንቢ የላቀ የዜማ ደራሲነት ሰብዕና መሠረታዊ ግንዛቤ ሊያስጨብጠን ቢችል ግን ጥቂቱን ብቻ ከዚህ እንደሚከተለው እዘረዝርላችኋለሁ፡—

ለአሊ ቢራና ሄለን በርሄ – “ሲያዴ”፤ ለፀሀዬ ዮሐንስ – “ማን ልበልሽ”፤ ለማዲንጎ አፈወርቅ – “ላላተርፍ”፤ ለብዙአየሁ ደምሴ – “የህልሜ ንግስት”፤ ለዘቢባ ግርማ – “ገራገር”፤ ለኢሳያስ ታምራት – “እያዳነ ያማል”፤ ለታረቀኝ ሙሉ – “ስሚያቸው”፤ ለሚኪያስ ቸርነት – “ግርማ ሞገሴ”፤ ለሃይማኖት ግርማ – “ከዚራ ቁ-2”፤ ለግርማ ተፈራ – “ልዩ”፤ ለሀመልማል አባተ – “ሀሴት”፤ እና የመሳሰሉቱን የአህመድ ዲንቢን የዜማ ፈጠራዎች ከብዙ በጥቂቱ ማስታወስ ይቻላል፡፡

አንዳንድ ሙዚቃዎች ለጆሮ ብቻ አይሰሩም፤ ለስሜት ይደርሳሉ፤ ዛሬ ተሰርተው ግን ትዝታችንን ይመልሱልናል፡፡

አንዳንድ ዜማዎች፣ በውስጣችን የተከረቸሙ የጊዜ በሮችን ያንኳኳሉ፤ ይከፍታሉምም፡፡ በሮቹ ሲከፈቱ ደግሞ የተዘነጉ ፊቶች፣ የተለየናቸው ጓደኞች፣ የተራመድንባቸውን ጎዳናዎች… ብቻ ምኑ ቅጡ ትላንታችንን እንደ መጽሀፍ ይገልጡልናል፡፡ በሆነ ዘመን የቀረውን ማንነታችንን እንደገና ይመልሱልናል።

አህመድ ተሾመ (ዲንቢ) ከ14 ዓመታት በኋላ በአዲስ አልበሙ ሲመለስ፣ እኔ የሰማሁት የአዳዲስ ዜማዎች ስብስብን አይደለም። አንድ በሆነ ዘመን የነበረ የዜማ ሰዋሰውና በዚሁ ዜማ ምክንያት የተሰፋ፣ የምናፍቀውን ዘመን የመለሰልኝ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡
ያ የኔ ዘመን የምለው “ዘጠናዎቹ”ን ነው፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኜ የገባሁት በ1997 ዓ.ም. ነው። አይ፣ ተማሪነት! እንዴት ያለ ጣፋጭ፣ እንዴት ያለ የማይደገም ዘመን ነበር! ያ ዘመን ለእኔ የወጣትነት ወርቃማ ጠዋት ነበር። ዓለምን እንደ አዲስ ማየት የጀመርኩበት፤ ከተማዋን፣ ሕይወትን፣ ፍቅርን፣ ሐሳብንና ነፃነትን ለመጀመሪያ ጊዜ በሙሉ ልብ ያጣጣምኩበት ዘመን ነበር።

ያ ዘመን ከጓደኞቸ ጋር እንደፈለግን የኖርንበት ዘመን ነበር። በአደባባይ የተከራከርንበት፣ አለምን የጠየቅንበት፣ መንግሥትን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቃወምንበት፣ ነፃነትን ያየንበት፣ ዜማን ያጣጣምንበት ወቅት ነበር። ያ ዘመን “ዘጠናዎቹ” ነበር፡፡

ያንን ዘመን ሁሌም እናፍቀዋለሁ፤ ምናልባትም የምናፍቀው ዘመኑን ራሱን አይደለም፤ በዚያ ዘመን ውስጥ የነበርነውን እሱን፣ እሷን፣እኔን፣እኛን ነው። እንደገና እንዲመጣም እመኛለሁ።

ማርሴል ፕሩስት የተባለ ፈረንሳያዊ የልብ ወለድ ጸሀፊና ሀያሲ ጥልቅ የሆነን ትዝታ አስበን ለማስታወስ በምናደርገው ጥረት አይመለስም፤ ነገር ግን የስሜት ሕዋሳችን በሚነካ አንድ ድንገተኛ ልምድ ሊቀሰቀስ ይችላል ይላል፡፡ ሙዚቃም ከእነዚህ የትዝታ ቀስቃሾች መካከል እጅግ ኃይለኛው ሳይሆን አይቀርም።

በዚህ ረገድ እንደ አህመድ ተሾመ ጥንቅቅ ተደርጎ የተሰራ ዜማ የተረሳ ግን ተደበቀ ስሜትን ይቀሰቅሳል፤ የጠፋ የሚመስለውን የዜማ ስልተ ምት ይመልሳል፤ በዘመን ጥላ ሥር ተደብቆ የኖረ ማንነት እንደገና ያነቃቃል።

በ1990ዎቹ የኢትዮጵያ ሙዚቃ የራሱ የሆነ የዜማ ሰዋሰው፣ ቀለምና የአወራረድ ለዛ ነበረው። ያ ዘመን ለእኔ ሙዚቃን ከመስማት ወደ ማዳመጥ የተሸጋገርኩበት ጊዜ ነው። ስለዚህ የዚያ ዘመን ዜማዎች በጆሮዬ ብቻ ተደምጠው አልቀሩም፤ በማንነቴ ውስጥ ህያው ናቸው።

እኔ የሙዚቃ ባለሙያ አይደለሁም፤ ሙዚቃን ግን በልቤ አዳምጠዋለሁ። በእኔ የዜማ አረዳድ፣ የዚያ ዘመን የዜማ አሠራሮች በቀላሉ የሚደገሙ አይደሉም። ምክንያቱም ዜማው የተፈጠረው በድምፅ ብቻ ሳይሆን፣ በዘመኑ መንፈስም ጭምር ነው። ከዚያ በኋላ የመጡት ዘመናት የራሳቸውን የሙዚቃ ቋንቋ ፈጥረዋል።

ያው ዘመን ሲለወጥ የዜማ ሰዋሰውም የሚለወጥ ይመስለኛል፡፡ ይህም የሥነ ጥበብ ተፈጥሯዊ ሂደት ነው፤ ዋናው ጉዳይ ግን በ1990ዎቹና ከዚያ በኋላ በመጡት ዜማዎች መካከል የተቋረጠ ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ መቆራረጡ ለሙዚቃ ባለሙያዎች ትልቅ የጥናት ርዕስ የሚሆንም ነው፡፡

ታዲያ የአህመድ ተሾመ አዲስ አልበም፣ የ1990ዎቹን የዜማ መንፈስ አገኘሁበት፤ የቀድሞውን በቀጥታ ሳይደግም፣ ያንን ለዛ በአዲስ ስልተ ምት የቀነበበ ዜማ ሆኖ አዳመጥኩት። ጉዳዩን ሳይንቲፊካሊ መግለጽ ባልችልም ልቤ ግን አልበሙ በዚያን ጊዜና በዛሬው የሙዚቃ ዘመን መካከል የተዘረጋ የዜማ ድልድይ እንደሆነ ይነግረኛል።

በአጠቃላይ ለእኔ፣ የአህመድ ተሾመ (ዲንቢ) ጊዜ አይሄድም አዲስ አልበም የአዳዲስ ዜማዎች ስብስብ ብቻ አይደለም። ካለፈ ጊዜና ትዝታ ጋር የተደረገ ውይይት ነው፤ ትናንትን ከዛሬ ጋር ያስታረቀ የዜማ ድልድይ ነው፤ በዘጠናዎቹ የቀረውን እኔን የመለሰ አልበም ነው። ይመችሽ ዲንቢ!!

ካላመናችሁኝ ደግሞ ከአዲስ አልበሙ መካከል “ጊዜ አይሄድም”፣”አይሽና”፣ “ይረፍዳል” እና “ህልም ነው” አድመጣችሁ ፍረዱኝ፤ ካጠፋሁ እኔ ሳልሆን ዲንቢ ይቀጣል፡፡




Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1