2019 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪ.ሜ. የጎዳና ላይ ሩጫ ምዝገባ በይፋ ተጀመረ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | የ2019 ዓ.ም. የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ሩጫ ምዝገባ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል። ውድድሩ እሑድ ህዳር 13 ቀን 2019 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት በታሪኩ ከፍተኛውን 60,000 ተሳታፊዎች ለመቀበል ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል።

በዚህ ዓመት ባንክ ኦፍ አሜሪካ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና አጋር (Presenting Partner) ሆኖ ስራውን የሚጀምር መሆኑም ተነግሯል።

ከ10 ኪ.ሜ. ውድድሩ በተጨማሪ፣ በአንድ ቀን ልዩነት የሚካሄደው የህጻናት ሩጫ በዚህ ዓመት 5,000 ህጻናትን ለማሳተፍ መታቀዱ ተገልጿል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዳግማዊት አማረ በምዝገባ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ ውድድሩ በወጣቶች ዕድል ፈጠራ፣ በስፖርት ቱሪዝም እና በአካባቢያዊ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ተፅዕኖ ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የዓለም ትልቁ 10 ኪ.ሜ. የጎዳና ላይ ሩጫ ለመሆን ያለውን ራዕይ አስቀምጠዋል።

ከሰሃራ በታች ለሚገኙ አገራት የባንክ ኦፍ አሜሪካ የበላይ ኃላፊ ይቮን ኢኬ በላኩት መልዕክት፣ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ማህበረሰቦችን የሚያቀራርብ፣ ወጣቶችን የሚያነሳሳ እና ኢትዮጵያን በዓለም የሚያስተዋውቅ ጠንካራ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

ውድድሩ ከ2017 ዓ.ም. ጀምሮ የወርልድ አትሌቲክስ ሌብል ዕውቅና ያገኘ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት 3,000 የመሮጫ ቦታዎች በነፃ ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መመደባቸውም ተገልጿል።

በ26 ዓመታት የውድድሩ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ “ከአንድ ሰዓት በታች እንሮጣለን” በሚል ምድብ ለሚመዘገቡ ተሳታፊዎች የሰዓት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ የሚተገበር ሲሆን፣ ተሳታፊዎች በአዲሱ የልምምድ መተግበሪያ (Training App) ተጠቃሚ እንዲሆኑም ጥሪ ቀርቧል።

በ2019 የታላቁ ሩጫ 10 ኪ.ሜ. ውድድር መሳተፍ የሚፈልጉ ግለሰቦች ምዝገባቸውን በቴሌብር መተግበሪያ ብቻ ማከናወን እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን፣ የዘንድሮው የውድድር መሪ ቃል “ሩጫዬ ቀለሜ” (My Run, My Color) መሆኑም ተነግሯል።






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: