በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው “ወርልድ ፐብሊክ ሰሚት አፍሪካ” ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሄደ!

- Advertisement -
Sidebar AD

#Fastmereja I የአፍሪካ ሕዝቦችን ቁርኝትና አህጉራዊ ትብብር ለማጠናከር ያለመውና በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው “ወርልድ ፐብሊክ ሰሚት አፍሪካ” (World Public Summit Africa) ጉባኤ በዛሬዉ እለት በአዲስ አበባ ተካሄደ።

«አዲስ ዓለም አፍሪካ የጋራ መፃኢ እድልን በመቅረጽ ረገድ» በሚል መሪ ቃል በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ECA) አዳራሽ በተካሄደው በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ ከ700 በላይ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የቢዝነስ ባለሀብቶች፣ የሲቪል ማህበራት ተወካዮች፣ ምሁራንና ወጣቶች ከመላው አፍሪካና ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ተሳትፈዋል።

ጉባኤው በስፖርት፣ በባህልና በትምህርት ዘርፎች ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ባተኮሩ አምስት የፓናል ውይይቶች የተከናወነ ሲሆን፤ አፍሪካ አዲስ በሚፈጠረው ዘብዙኃን ዓለም አቀፍ ሥርዓት (Multipolar World) ውስጥ ያላትን ማዕከላዊ ሚና የሚያንፀባርቅና በ”ኡቡንቱ” የፍልስፍና መርህ ላይ ያተኮረ ምክክር ተደርጎበታል።

በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063ን ለማሳካት የሚረዳ “የአፍሪካ ኮሙኒኬ” (African Communiqué) የጸደቀ ሲሆን፣ ሶስት ዋና ዋና አህጉራዊ ፕሮጀክቶችም ይፋ ሆነዋል።

ከእነዚህም መካከል አንጎላ፣ ዚምባብዌ፣ ዛምቢያ፣ ናሚቢያ፣ ቦትስዋና እና ሞዛምቢክን የሚያስተሳስረው «የዛምቤዚ ወንዝ፡ ኢኮኖሚ፣ ማህበረሰብ እና መንፈስ» በሚል ርዕስ የቀረበው ሳይንሳዊ ጥናት ይገኝበታል። በተጨማሪም በሕዝብ ዲፕሎማሲ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ 10 አፍሪካውያን ልዩ እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።

ጉባኤው የእውነተኛ አንድነትን በማሳየት ለሁሉም የዓለም ሕዝቦች የሚሰራ አዲስ ዓለም ለመገንባት መንገድ የሚጠርግ ሲሆን የአዲስ አበባው ጉባኤ በመጪው መስከረም ወር በሞስኮ ለሚካሄደው ሁለተኛው የዓለም የህዝብ ለህዝብ ጉባኤ የአፍሪካን አቋም ያዘጋጀበት መድረክ መሆኑ ተገልጿል።

የጉባኤው አካል የሆነውና ከ16 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ታዋቂ አርቲስቶች ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት «አንድነት» (Unity) የተሰኘ ዓለም አቀፍ የኪነ-ጥበብ ኤግዚቢሽን በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መከፈቱ ታውቋል።

ይህ አህጉራዊ መድረክ መቀመጫውን በሩሲያ ሞስኮ ባደረገው “ወርልድ ፒፕልስ አሴምብሊ” (World Peoples Assembly) ከአገር በቀልና ዓለም አቀፍ አጋሮቹ ሰርቨ ግሎባል እና ግሎባል ብላክ ሴንተር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1