አፍሪካ አዲሱን የዓለም ሥርዓት በመቅረጽ ረገድ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን እንዳለባት ተነገረ

- Advertisement -
Sidebar AD

#ethiopia | የአፍሪካ ሀገራት እርስ በእርስ ከሩሲያ እና ከተቀረው ዓለም ጋር ያላቸውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመውና በአህጉሩ የመጀመሪያው የሆነው የአለም ህዝቦች ቀን መካሄድ ጀመረ።

ይህ ጉባኤ ከ700 በላይ ተሳታፊዎችን ከ400 በላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት ተወካዮች አምባሳደሮች እና የመላው አፍሪካ ወጣቶችን በአንድ ላይ ያገናኘ ትልቅ ሁነት ነው።

​በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የግሎባል ብላክ ሴንተር ዋና ጸሐፊ ጸጋዬ ጫማ አዲስ አበባ የአፍሪካ የፖለቲካ መዲና እና የነጻነት የጽናትና የዲፕሎማሲ ተምሳሌት በመሆኗ እንዲህ ዓይነቱን አህጉራዊ ጉባኤ ለማስተናገድ ተገቢዋ ስፍራ መሆኗን ገልጸዋል።

አክለውም አፍሪካ በበለጸገ ባህሏ በተፈጥሮ ሀብቷ እና በወጣት ኃይሏ አዲሱን የዓለም ሥርዓት በመቅረጽ ረገድ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን እንዳለባት አስምረውበታል።

አቶ ​ጸጋዬ በንግግራቸው የአፍሪካውያንን የጋራ እሴት የሚያንጸባርቀውን የ”ኡቡንቱ” ፍልስፍና ያነሱ ሲሆን፣ “እኔ ስላለን ነኝ” የሚለው ይህ ጥበብ ለዓለም ሕዝቦች ትስስርና ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።

ጉባኤው ወጣቶችና ሴቶች የራሳቸውንና የአህጉራቸውን መጪ እድል በባለቤትነት እንዲመሩ የማስቻል ዓላማ ያለው መሆኑንም አብራርተዋል።

​በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒይ ቴሬክሂን በበኩላቸው አዲሱ የብዙ-ዋልታ ዓለም አደረጃጀት በመንግስታት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በሲቪል ማህበራት እና በሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ጭምር የሚገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

ሩሲያ ከአፍሪካ የሲቪል ማህበራት ጋር በትምህርት፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በባህል ዘርፎች የጠበቀ ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም ገልፀዋል።

​አምባሳደሩ አክለውም ጉባኤው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የኢንፎርሜሽን ኤኮሲስተምን መጠበቅ፣ የወጣቶች ዲፕሎማሲ መረብን ማጠናከር እና የሰው ሰራሽ አስተዋጽኦ (AI) ተጽዕኖዎችን መጋፈጥ ባሉ ተግባራዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል።

የግሎባል ብላክ ሴንተር እና የሩሲያ ትብብር የአፍሪካን ባህላዊ ማንነት ከውጭ ጎጂ ተጽዕኖዎች ለመጠበቅ ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።

​ይህ ጉባኤ መቀመጫውን በሞስኮ ካደረገው “ወርልድ ፒፕልስ አሴምብሊ” በተጨማሪ ከግሎባል ሰርቭ እና ከግሎባል ብላክ ሴንተር ጋር በትብብር የተዘጋጀ ነው።

በስብሰባው ላይ በባህል በትምህርት፣ በወጣቶች፣ በቅርፅ እና በልማት ዙሪያ ከ20 በላይ የፓናል ውይይቶች የሚካሄዱ ሲሆን፣ የትምህርት፣ የሲቪል ማህበራት እና የቢዝነስ ተቋማት ተወካዮች ይሳተፉበታል።

ሔኖክ ወ/ገብርኤል

#Ethiopia #GetuTemesgen #GetuNews
#Workdpublicsummit
#globalblackcentre






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1