የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖልና ከማላዊ ፖሊስ ጋር በመተባበር በአደገኛ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪነት ወንጀል የተጠረጠረ

- Advertisement -
Sidebar AD

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖልና ከማላዊ ፖሊስ ጋር በመተባበር በአደገኛ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪነት ወንጀል የተጠረጠረውን አድነው ባሻው ውዳሞን በማላዊ በቁጥጥር ሥር በማዋል ወደ ኢትዮጵያ አምጥቷል።

ተጠርጣሪው ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን በተለይም ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከሀድያ እና ከንባታ ዞኖች በርካታ ወጣቶችን ሕይወታቸውን እንደሚያሻሽል በመሐላና በአጉል ተስፋ በማታለል ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲያዘዋውር መቆየቱ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ተረጋግጧል።

ተጓዦችን ከ600 ሺህ እስከ 800 ሺህ ብር ያስከፍል የነበረ ሲሆን፣ በቅድመ ክፍያ በኢትዮጵያ እስከ 100 ሺህ ብር እና ከዚያ በላይ በባንክ ይቀበል እንደነበር የምርመራ መዝገቡ ያመላክታል።

ተጓዦቹን በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ ካሻገረ በኋላ በጋንቦ ጫካ ውስጥ በድብቅ በማስቀመጥ በየ24 ሰዓቱ ትንሽ ሩዝ ከቁራጭ ዳቦ ጋር ብቻ በመስጠት ለከፍተኛ ረሃብና የውሃ ጥም የዳረጋቸው ሲሆን፣ በሞተርና በእግር ሴሎ በረሃን እንዲያቋርጡ አስገድዷቸዋል።

ናይሮቢ ካደረሳቸው በኋላም በአንድ ክፍል ውስጥ በማጎር ከቤተሰቦቻቸው ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያስልኩ በማስገደድ፣ ገንዘብ ማስላክ ያልቻሉትን በዱላ በመደብደብና በኤሌክትሪክ ንዝረት በማሰቃየት ተጨማሪ ገንዘብ በኢትዮጵያ ባሉ ግብረ አበሮቹ በኩል እንዲከፈለው አድርጓል።

በተጨማሪም ተጓዦቹን ከናይሮቢ ወደ ሞምባሳና ታንዛኒያ በዕቃ መጫኛ ኮንቴነሮች፣ በተሳቢና በሸራ በተሸፈኑ መኪኖች ውስጥ አጉሮ በመጫን ታንዛኒያ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ጥሏቸው የተሰወረ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ወጣቶች ደቡብ አፍሪካ ሳይደርሱ በተለያዩ ሀገራት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው እስከ ሦስት ዓመት እስራት ከተቀጡ በኋላ እስከ 170 ሺህ ብር ከፍለው ወደ ሀገር መመለሳቸው ተገልጿል።

ፌደራል ፖሊስ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪውን በማላዊ ፖሊስ አስይዞ ሐምሌ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ተረክቦ ወደ ሀገር ያመጣው ሲሆን፣ ህብረተሰቡ በEFPApp፣ በ991 እና በSPS ጥቆማ በመስጠት ትብብሩን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።






Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: