#Ethiopia | በአርሲ ዞን አሰላ ከተማ በሚገኙት ኦዳ እና የ80 ዓመታት ዕድሜ ባለው አንጋፋው ጭላሎ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በ15 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ ሁለት የታዳጊ ሴት ልጆች ማቆያ ማዕከላት በይፋ ተመረቁ።
‘እሸት የሕፃናትና ወጣቶች ልማት ድርጅት’ ከ‘ጉድ ፒፕል ኢንተርናሽናል’ ጋር በመተባበር በጥራትና በሁለት ወራት አጭር ጊዜ ውስጥ ያስገነባቸው እነዚህ ማዕከላት ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሴት ተማሪዎችን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው።
እነዚህ ማዕከላት ታዳጊ ሴት ልጆች ከጥቃት፣ ከመድልዎና ከጎጂ ልማዶች ነፃ በሆነ አካባቢ የትምህርት ገበታቸውን እንዲከታተሉ ከማስቻላቸውም በላይ የስነ-ልቦና ድጋፍ፣ የማማከር አገልግሎትና የሕይወት ክህሎት ስልጠናዎችን የሚያገኙበት ምቹ ስፍራ ይሆናሉ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ እንደገለጹት ማዕከላቱ ተማሪዎችን በትምህርታቸው ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ተማሪዎችን በውሳኔ ሰጪነት በስልጠና እና በሜንተርሺፕ የማብቃት ሰፊ ተግባራት የሚከናወኑባቸው የልህቀት ማዕከላት ናቸው።
የአሰላ ከተማ ከንቲባ አቶ ፀጋዬ በጅጋ በምረቃው ወቅት ባደረጉት ንግግር ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው የሴት ተማሪዎችን ነገ ማብቃት ከተማዋ ከያዘችው አጠቃላይ የመሰረተ ልማት እና የዕድገት ራዕይ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መሆኑን ገልጸዋል።
“ታዳጊዋ ኢትዮጵያ” በመባል የምትታወቀው አሰላ የነገ ተስፋዎቿን ለማብቃትና የመሪነት ብቃታቸውን ለማሳደግ የምታደርገው ጥረት ከተማዋ ከጀመረቻቸው ታላላቅ የመሰረተ ልማትና የቱሪዝም ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን የሰው ሀብትን ለመገንባት የተጣለ ትልቅ መሠረት መሆኑ ተመልክቷል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu



Source: GetuTemesgen









No comments yet.