#FastMereja I የጤና ሚኒስቴር፣ የኢፌዴሪ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን እና ተጠሪ ተቋማት የኅብረተሰቡን ጤና ከመጠበቅና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዙ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ያለሙ የአረንጓዴ አሻራና የክረምት የበጎ አድራጎት መርሃ-ግብሮችን በይፋ አስጀመሩ።
በዛሬው ዕለት በቢሾፍቱ በተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ከ5ሺህ በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ በጤናው ዘርፍ በአጠቃላይ ከ250 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ደኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ተናግሯል። ይህ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ በ2027 እ.ኤ.አ ለምታስተናግደው 32ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ዝግጅት አካል መሆኑ ተገልጿል።
ለአገር በቀል፣ ለፍራፍሬ እና መድኃኒትነት ላላቸው ተክሎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የተካሄደው ይህ ተከላ፣ አገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን የሕክምና ጥሬ ዕቃ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ለያዘችው ስትራቴጂካዊ ግብ ትልቅ መነሻ እንደሚሆን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ ተናግሯል።
በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች የገበያውን 44 በመቶ አቅርቦት የሚሸፍኑ ቢሆንም፣ አብዛኛው ጥሬ ዕቃ ከውጭ የሚገባ በመሆኑ መድኃኒትነት ያላቸውን ተክሎች በስፋት ማልማትና ወደ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር ወሳኝ እንደሆነ ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት የሚያከናውነውን የቁጥጥር ሥራ ጎን ለጎን «ጤናማ ምግብ ለአስተማማኝ ሕይወት፤ አረንጓዴ ልማት ለነገ ትውልድ!» በሚል መሪ ቃል የክረምት የበጎ አድራጎት ሥራዎቹን በይፋ ማስጀመሩን የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ ገልጸዋል።
በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው በዚህ መርሃ-ግብር የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች እና የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች በተገኙበት የችግኝ ተከላና የእንክብካቤ ሥራ ተከናውኗል። ከተተከሉ በኋላም አስፈላጊው ክትትል እንዲደረግላቸው ቋሚ አሰራር እንደተዘረጋም ተነግሯል።



Source: FastMereja









No comments yet.