የ5 ዓመቱ የትምህርት ሪፎርም፦ ምን ተሰራ? ምን ተለወጠ?

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት የተካሄደው የትምህርት ሪፎርም በሥርዓተ ትምህርት፣ በመሠረተ ልማት፣ በትምህርት ጥራት እና በዲጂታል አገልግሎት ዘርፎች ጉልህ ለውጦችን ማስመዝገቡን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ እንደገለጹት፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ የትምህርት ጥራትን የሚያሻሽል አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተተግብሯል፤ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፤ በተለይ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ለማብቃት የሚያገለግሉ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችም ተቋቁመዋል።

በመሠረታዊ ትምህርት ዘርፍ የመማሪያ መጻሕፍትን “አንድ ተማሪ አንድ መጽሐፍ” (1፡1) በሚል መርህ ለተማሪዎች ማዳረስ መቻሉ ተጠቅሷል።

እንዲሁም የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር ሽፋን በስፋት መጨመሩ የትምህርት ተሳትፎን እና የተማሪዎችን የመማር አቅም ለማጠናከር አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ተገልጿል።

ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከኩረጃ ነፃ እንዲሆን የበይነ መረብ (Online) ፈተና ሥርዓትን ማስፋፋት ከተሳኩ ለውጦች አንዱ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ይህም የፈተናዎችን ተዓማኒነት ለማሳደግ እና የትምህርት ሥርዓቱን ተጠያቂነት ለማጠናከር እንደረዳ ተገልጿል።

በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍም የዩኒቨርሲቲዎች አስተዳደር በብቃት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ሥርዓት መዘርጋቱ፣ የዩኒቨርሲቲ ቦርዶችና አመራሮች ከአካባቢያዊ ተፅዕኖ ውጪ በብቃት እንዲመረጡ መደረጉ እና ተቋማት በተልዕኳቸውና በልዩ ተልእኳቸው መሠረት እንዲመሩ መደረጉ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም 9 ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር ለመሸጋገር በሂደት ላይ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ የተቋማቱን ተጠያቂነት፣ ውጤታማነት እና የውሳኔ አሰጣጥ ብቃት እንደሚያሳድግ ተጠቁሟል።

የትምህርት ሚኒስቴሩ በዲጂታል ሽግግር ረገድም 22 የሶፍትዌር ሥርዓቶችን በራሱ አቅም በማበልጸግ የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመንና ማቀላጠፍ መቻሉን ገልጿል።

ይህም በመረጃ አያያዝ፣ በተማሪዎች እና በመምህራን መረጃ ሥርዓት፣ እንዲሁም በአስተዳደራዊ ሥራዎች ቅልጥፍናን ለማሳደግ አስችሏል።

ሚኒስቴሩ በመጪዎቹ ዓመታትም የተጀመሩትን የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ሥራዎች ይበልጥ በማጠናከር፣ ተደራሽነትን በማስፋት፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በማጠናከር እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ውጤታማነት በማሳደግ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አረጋግጧል።


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2