አሜሪካ የቪዛ ዋስትና ክፍያን ቋሚ አደረገች፣ ተጓዦች እስከ 20 ሺህ ዶላር ይጠየቃሉ!

- Advertisement -
Sidebar AD

​#FastMereja I የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች 30 የአፍሪካ ሀገራት ጨምሮ የ50 ሀገራት ዜጎች ወደ ሀገሪቱ ለንግድና ለጉብኝት (B1/B2) ቪዛ ሲያመልክቱ እስከ 20 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የቪዛ ዋስትና (Visa Bond) ማስያዝ የሚያስገድደውን መመሪያ በቋሚነት ማጽደቁን አስታወቀ።

​ቀን፦ ነሐሴ 1 ቀን 2018 ዓ.ም. (August 1, 2026)

​እንደ አዲሱ መመሪያ አሰራር፣ ተጓዦች የተሰጣቸውን የቪዛ ጊዜ ሳያሳልፉ እና የሀገሪቱን ህግ አክብረው ከተመለሱ ያስያዙት ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ተመላሽ ይደረግላቸዋል። ነገር ግን ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ የሚቆዩ ወይም የቪዛ ደንብ የሚጥሱ ከሆነ ያስያዙት ገንዘብ ለመንግስት ገቢ እንደሚሆን ተገልጻል።

​ይህ አሰራር ቀደም ሲል ለሙከራ ትግበራ ተዘርግቶ የነበረ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባደረገው ግምገማ ከቪዛ ጊዜ በላይ የመቆየት ችግርን በመቀነስ ረገድ ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱ በቋሚነት ስራ ላይ እንዲውል ተወስኗል። የቆንስላ ክፍሎች እንደ አመልካቾቹ ሁኔታ ከ10 ሺህ፣ 15 ሺህ እስከ 20 ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በዋስትና መልክ እንዲያዝ የመወሰን ስልጣን ተሰጥቷቸዋል።

​በዚህ መመሪያ ውስጥ የተካተቱት የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ቤኒን፣ ቦትስዋና፣ ቡሩንዲ፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኮትዲቯር፣ ጅቡቲ፣ ጋቦን፣ ጋምቢያ፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ሌሶቶ፣ ማላዊ፣ ሞሪታኒያ፣ ሞሪሸስ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ፣ ሴኔጋል፣ ሲሼልስ፣ ታንዛኒያ፣ ቶጎ፣ ቱኒዚያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ ናቸው።

​የአሜሪካ ባለስልጣናት እርምጃው የህገ-ወጥ ስደተኞችን ቁጥር እና የቪዛ ጊዜ ማለፍን ለመግታት ያለመ ነው ሲሉ ቢገልጹም፣ የስደት ህግ አዋቂዎችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ግን አሰራሩ ህጋዊ ተጓዦችን እንደሚያሰናክልና ከፍተኛ የፋይናንስ ጫና እንደሚፈጥር በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2