የቆማ ፋሲለደስ (ደብረ አንፆኪያ) ቤተክርስቲያን – የታሪክ፣ የእምነትና የቅርስ መዲና

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን በእስቴ ወረዳ፣ ከእስቴ ከተማ በ52 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የቆማ ፋሲለደስ (ደብረ አንፆኪያ) ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ያላት ጥንታዊ የእምነትና የባህል ማዕከል ናት።

ደብሩ በ1597 ዓ.ም. በእቴጌ ወልደ ሳህላ፣ የአፄ ሱስኒዮስ (ስልጣን ሰገድ) ባለቤት ተመሠረተ። በኋላም አፄ ፋሲለደስ በንግሥናቸው ስምንተኛ ዓመት በእናታቸው አሳሳቢነት ደብሩን በ«ርዕሰ አድባራት ወገዳማት» ማዕረግ በማክበር ከፍተኛ መንፈሳዊ ሥልጣንና ክብር ሰጥተውታል።

ቤተክርስቲያኑ በክብ ቅርጽ የተገነባ ሲሆን፣ በ26 ዓምደ ወርቅ የተደገፈና በቀይ ድንጋይ (ቦዝ) የተሠራ ውብ ሕንፃ ነው። በቅፅሩ ውስጥ የትምህርት ቤት፣ ጉባኤ ቤት፣ እንዲሁም በፋሲል ግንብ አቀማመጥ የተሠራ የዕቃ ቤትና የደወል ማማ ይገኛሉ።

የደብሩ አስተዳደራዊና ሥርዓተ አገልግሎት በ318 ሊቃውንት የተዋቀረ ሲሆን፣ መምህራን፣ ሊቃውንት፣ መርጌታዎች፣ መነኮሳት፣ ደብተራዎችና ሌሎች በርካታ አገልጋዮችን ያካተተ ሥርዓት ነበረው።

ደብሩ በተለይ በ«ቆሜ ፀዋት ዜማ» ይታወቃል። ይህ ዜማ ከቅዱስ ያሬድ የወረሰ ጥንታዊ የቅዳሴ ዜማ መሆኑ ይነገራል። በዮዲትና በአህመድ ግራኝ ዘመን ብዙ ቤተክርስቲያናት በተጎዱበት ወቅትም ይህ የያሬድ ዜማ በደብሩ ሳይቀየር እስከ ዛሬ መጠበቁ የቤተክርስቲያኑ ልዩ መለያ ነው።

የቆማ ፋሲለደስ ቤተክርስቲያን በውስጧ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከእብነበረድና ከሌሎች ውድ ማዕድናት የተሠሩ ንዋያተ ቅድሳትን የያዘች ሲሆን፣ ለእስቴ ወረዳ፣ ለአማራ ክልል እና ለመላው ኢትዮጵያ ጠቃሚ የታሪክ፣ የሃይማኖትና የቱሪዝም መዳረሻ ሆና ትገኛለች።

የእስቴ ወረዳ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽሕፈት ቤት




Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2