#Ethiopia | በስዊድን ጎተንበርግ በተካሄደው የ2026 የጎቲያ ካፕ የዓለም አቀፍ የታዳጊዎች እግር ኳስ ውድድር ላይ ከተሳተፉ በኋላ ደብዛቸው የጠፋው ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በገዛ ፈቃዳቸው መሄዳቸውንና በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት የወንጀል ወይም የሰው ህገወጥ ዝውውር ምልክት እንዳልተገኘ የስዊድን ፖሊስ አስታወቀ።
ከሀምሌ 12 እስከ 18 በተካሄደው በዚህ ውድድር ላይ ሲሳተፉ የቆዩትና ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 17 ዓመት የሚሆኗቸው አብዛኞቹ ታዳጊዎች ከአንድ አዋቂ የቡድን መሪያቸው ጋር በድምሩ ወደ 20 የሚጠጉ የቡድኑ አባላት ያረፉበትን ትምህርት ቤት ለቀው የተሰወሩት በውድድሩ የመጨረሻ ቀን ነበር።
የውድድሩ አዘጋጆች ቡድኑ ማደሪያውን ያለ ምንም ቅድመ ማሳወቂያ ለቆ መሄዱን ከተረዱ በኋላ ወዲያውኑ ለፖሊስ ጥቆማ ማድረሳቸው ታውቋል።
የስዊድን ፖሊስ ከአስፈላጊ አካላት ጋር በመተባበር የቡድኑ አባላት ያሉበትን አድራሻ ለማወቅ ጥረቱን የቀጠለ ሲሆን እስካሁን ግን ምንም ዓይነት ሕገ-ወጥ ድርጊት ስለመፈጸሙ የሚያሳይ ማስረጃ እንደሌለ ገልጿል።
የኢትዮጵያው ክለብ ተወካይ ተጫዋቾቹ በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘታቸውን ለስዊድን መገናኛ ብዙኃን የገለጹ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ያሉበትን ትክክለኛ ቦታ ወይም ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን ግን ከማረጋገጥ ተቆጥበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ በክስተቱ ማዘኑን ገልጾ ቡድኑ በራሱ መንገድ ባመቻቸው ጉዞ የተሳተፈ እንጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ወክሎ እንዳልተጓዘ አብራርቷል።
አክሎም ህዝቡ ታዳጊዎቹ የብሔራዊ ቡድን አባላት እንደሆኑ አድርገው የሚያቀርቡ የተሳሳቱ ዘገባዎችን እንዳይቀበል አሳስቧል።
በያፌት ገ/ህይወት
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu
Source: GetuTemesgen









No comments yet.