በፔሩ የቱሪስት አውሮፕላን ተከስክሶ 13 ሰዎች ሞቱ

- Advertisement -
Sidebar AD

ፔሩ ውስጥ ቱሪስቶችን ጭኖ ሲበርር የነበረ አነስተኛ አውሮፕላን ተከስክሶ፣ በውስጡ የነበሩት 13 ሰዎች በሙሉ ሕይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ ባለሥልጣናት እና መገናኛ ብዙኃን ገለጹ።
‘ሴስና ካራቫን ሲ-208’ የተባለው አውሮፕላን ቅዳሜ ዕለት የተከሰከሰው ‘ናዝካ ላይንስ’ በተሰኘው አርኪኦሎጂ ስፍራ በኩል እየበረረ በነበረበት ወቅት ነው። አውሮፕላኑ 11 ተሳፋሪዎች እና ሁለት ፓይለቶች ይዞ ነበር።
ከተሳፋሪዎቹ መካከል ሁለት ጀርመናውያን፣ ሁለት የስፔን ዜጎች እና ሰባት ጣሊያናውያን ቱሪስቶች እንደነበሩ የፔሩ የመንግሥት የዜና ወኪል ዘግቧል። አደጋው የደረሰበት ምክንያት እስካሁን አልታወቀም።

በደቡባዊ ፔሩ የሚገኘው ‘ናዝካ ላይንስ’፣ በበረሃ አሸዋ ላይ የተሳሉ ጥንታዊ የእንስሳት ስዕሎች የሚታዩበት እና በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ታዋቂ የቱሪስት ስፍራ መስህብ ነው።
ብዙውን ጊዜ ቱሪስቶች ስዕሎቹ ምን ያህል ስፋት ያለው ስፍራ ላይ እንዳረፉ ለመመልከት በአነስተኛ አውሮፕላኖች ይበራሉ

የፔሩ ፖሊስ አመራሩ ሜጀር ጆርጅ አንደራዴ “ከአደጋው አስከፊነት የተነሳ በሕይወት የተረፈ ሰው የለም። እስካሁን የአራት ሰዎችን አስከሬን አግኝተናል” ማለታቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
‘ፒስኮ’ በተባለው የፔሩ ከተማ ከሚገኝ አየር ማረፊያ የተነሳው አውሮፕላን የተከሰከሰው ፑዌብሎ ቪየሆ የተባለው ክልል ውስጥ ነው።
የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ባወጣው አንድ ቪዲዮ ላይ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ከስብርባሪዎች ጭስ የሚወጣበት የአደጋ ስፍራ ላይ ውሃ ሲረጩ ያሳያል።
‘ዴ ናስካ’ ግዛት አስተዳደር ባወጣው መግለጫ አውሮፕላኑ ‘ኤሮዲያና’ የተሰኘው የፔሩ የአገር ውስጥ አየር መንገድ ንብረት መሆኑን አስታውቋል።
አየር መንገዱ በበኩሉ ጉዳዩ “የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ከሚያወጧቸው መመሪያዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ የበረራ መርሃ ግብሩን እንደሚገመግም” መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል።

ይህ ታዋቂ የቱሪስት መስህብ ባለፉት አስርት ዓመት ውስጥ ሌሎች የአውሮፕላን አደጋዎችንም አስተናግዷል።
በአውሮፓውያኑ 2022 አንድ አነስተኛ የቱሪስት አውሮፕላን በናዝካ ላይስ በኩል ሲበርር ተከስክሶ ሰባት ተሳፋሪዎች ሞተዋል።
2010 ላይ ደግሞ ሌላ የቱሪስት አውሮፕላን ወድቆ ተሳፍረው የነበሩ ስድስት ሰዎችን ገድሏል።

BBC



Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: