ሁለተኛው የስልጣን ዘመኔ ልክ እንደ ኢየሱስ መመለስ ነው!

- Advertisement -
Sidebar AD

– የፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ንግግር በኬንያ አነጋጋሪ ሆነ

አዲስ አበባ – የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ሁለተኛ የስልጣን ዘመንን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛ መምጣት ጋር በማያያዝ የተናገሩት ንግግር በኬንያ የፖለቲካ እና የሃይማኖት ውይይቶችን አቀጣጥሏል።

ፕሬዚዳንቱ በናይሮቢ ጊኮምባ በተካሄደ የቤተ ክርስቲያን መርሃ ግብር ላይ ለደጋፊዎቻቸው የፖለቲካ መፈክር የሆነውን “Tutam” በመጥቀስ፣ “ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ ይመጣል፤ ስለዚህ ‘Tutam’ ስትሉ ለዚያም ዝግጁ ሁኑ” በማለት ንግግር አድርገዋል።

እንዲሁም “ምድራዊ Tutam አለ፣ ሰማያዊ Tutam አለ” በማለት የፖለቲካ መፈክሩን ከክርስቲያናዊ ትምህርት ጋር ለማገናኘት ሞክረዋል።

ይህ ንግግር በማኅበራዊ ሚዲያ ፈጣን ምላሽ አስከትሏል። አንዳንዶች ፕሬዚዳንቱ የመንፈሳዊ መልእክት ለማስተላለፍ እንደሞከሩ ሲገልጹ፣ ሌሎች ግን የሃይማኖት ምሳሌዎችን ለፖለቲካ ዘመቻ መጠቀም ተገቢ አይደለም ሲሉ ተችተዋል።

“Tutam” የሚለው ቃል በሩቶ ደጋፊዎች መካከል “ሁለተኛ ዘመን እናሸንፋለን” የሚል የፖለቲካ መፈክር ሲሆን፣ ተቃዋሚዎቹ ደግሞ “Wantam” (አንድ ዘመን ብቻ) በሚል መፈክር ለ2027 ምርጫ ዘመቻቸውን እያጠናከሩ ነው። ይህም በኬንያ ፖለቲካ ውስጥ በጣም አነጋጋሪ የሆኑ መፈክሮች ሆነዋል።

የ2027 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እየተቃረበ በመምጣቱ፣ ሩቶ ሁለተኛ ዘመን ለማሸነፍ በግልጽ እየዘመቱ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎቻቸውም “Wantam” በሚል መፈክር የስልጣን ለውጥ እየጠየቁ ነው። የፖለቲካ ውድድሩ ቀድሞውኑ ወደ ከፍተኛ ሙቀት ገብቷል።

የሩቶ የቅርብ ጊዜ ንግግር ደግሞ በኬንያ ውስጥ የፖለቲካና የሃይማኖት ግንኙነት እንደገና የውይይት ርዕስ እንዲሆን አድርጎታል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: