“ታሪክ በትዝታ ላይ የተጫነ ሸክም አይደለም-የነፍስ መገለጥ እንጂ”

- Advertisement -
Sidebar AD

ጋዜጠኛ ዮናስ አየለ እንደጻፈው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከአሚኮ ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ አዳምጬ እንደጨረስኩ በቃለ ምልልሱ በርዕሰ ጉዳይ ደረጃ ጎልተው ከወጡ ዋና ዋና ጭብጦች መካከል አንዱ ነገረ ታሪክ እንደሆነ ተሰምቶኛል፡፡ ታሪክ-የሀገር ውስጥና የውጭ፤ የሩቅና የቅርብ ዘመን! ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቃለ ምልልሳቸው ያንጸባረቁትን ሚዛናዊና አምክኖአዊ የታሪክ እይታና ድምዳሜያቸውን አለማድነቅ ንፉግነት ነው፡፡ የአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን እንግሊዛዊ የታሪክ ጸሐፊና ፖለቲከኛ ሎርድ አክተን “History is not a burden on the memory but an illumination of the soul” ብሎ ሲጽፍ “ታሪክ የነፍስ መገለጥ እንጂ በትዝታ ላይ የተጫነ ሸክም አይደለም” ማለቱ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቃለ ምልልሳቸው ያነሷቸው የታሪክ አንኳር ጉዳዮች እስከዛሬ ድረስ በሀገራችን የታሪክ አጻጻፍ(Historiography) እና በሕዝባዊ ትርክቶቻችን(በሚዲያዎችን ጭምር) በሚገባቸው ልክ ያልተወሱ፤ ቢወሱም ፈራ ተባ እየተባሉ የሚጠቀሱ፤ አለፍሲልም ባልተገባ የፖለቲካ እይታ ደንቃራ ተደርገው የተወሰዱ የታሪክ ግርዶሽ(eclipse of the history) ሆነው የኖሩ ስብራቶቻችን ነበሩ፡፡ ከነዚህ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ዋነኛዎቹ አንዱ የሕዝቦች ትስስር እና መስተጋብር ታሪክ ሲሆን ሌላኛው በአገረ መንግስት ምሥረታ ውስጥ የሸዋ ጂኦ-ስትራቴጂካዊ ሚናን የተመለከቱት ናቸው፡፡

በመጀመሪያ የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች በኩታ ገጠም ቀዬዎቻቸው እና የታሪክ እድል በፈጠረላቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የባህል አጋጣሚዎች እንደሌሎች ማህበረሰቦች ሁሉ መጋባት መዋለዳቸው፤መተሳሰር መዋሀዳቸው ሀቅ የመሆኑን ያህል የታሪክ ጥናት እና የትርክቶቻችን ማጠንጠኛ አለመሆናቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ በባሰ ሁኔታ ደግሞ በነገሥታቱ መካከል የነበረው የፖለቲካ ጋብቻና የመሪዎቻችን ማህበራዊ መሠረት ጉዳይ ነውር እስኪመስል በእውነታው ልክ ሳይጠናና፣ሳይነገርለት ዘመናት አልፈዋል ፡፡ በሌላ በኩል በሸዋና አካባቢው ለረዥም ዘመን የኖሩ ሕዝቦች በአገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት የተጫወቱት ሚናና የሚጋሩት ቀደምት የሥልጣኔ ባለቤትነት (ታሪክ ሰሪነት-Agency) ግጥምጥሞሽ በሀገር መሪ ደረጃ መወሳታቸው እጅግ ጉልህ ፋይዳ ያለው ጉዳይ ነው ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቃለ ምልልሳቸው ያነሷቸው የታሪክ እውነታዎች ያለጥርጥር ታሪካችንንና የታሪክ ምልከታችንን ደጋግመን መመርምር እንዳለብን የሚያስገነዝቡና የወገንተኝነት ጥያቄ በሚነሳባቸው ሃይማኖታዊ የታሪክ ምንጮች እንኳን የተቀመጡ ገሃድ እውነታዎች ናቸው፡፡ መመርመር ለሚፈልግ አጥኚ እነዚህ የታሪክ እውነታዎች በየነገሥታቱ ዜና መዋዕሎች (የዐጼ አምደ ጽዮን፣ ዐጼ ሱስንዮስ፣የዐጼ ገላውዲዮስ፣ የዐጼ ሠርጸ ድንግል ወዘተ)፤ የሃይማኖት ሰነዶች፣ የታሪከ ነገሥት ቅጂዎች፣ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩ አውሮፓውያን ተጓዦችና ጸሐፊያን (ፍራንስስኮ አልቫሬዝ፣ ፔድሮ ፔዝ፣ ማኑኤል አልሜዳ፣ ጄሮኒሞ ሎቦ፣ ጀምስ ብሩስ፣ ኮንቲ ሮሲኒ ወዘተ ) መዝግበው በተውልን ሰነዶች ሰፍረው የምናገኛቸው፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የኖሩ ቱባ መረጃዎች ናቸው፡፡

ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ የተወልን የጽሑፍ ሰነድና ሌሎች ሀገርኛ የቃል መረጃ ምንጮች ዐፄ ልብነድንግል(1498-1532 ዓ.ም.) እንደ መሪ የአማራና የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ምናልባትም የሌሎች ሕዝቦችም ማህበራዊ ዳራ የነበራቸው ንጉሠ ነገሥት እንደሆኑ የሚያስረዱ ሲሆን አልቫሬዝ የንጉሱ የእናት ወንድም የነበሩት አጎታቸው ዶሪ ባህረ ነጋሽ ኦሮሞ እንደነበሩና ባህረ ነጋሽ ዶሪ ሲሞቱ ሥልጣኑ በቀጥታ ወደልጃቸው ቡሎ መሸጋገሩን ጭምር በአይኑ ያየውን ጽፏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በትኩረት መታየት የሚገባው ጉዳይ ስለዐጼ ልብነ ድንግል የጦር አዛዦች የተነገሩ የቃል መረጃዎች ናቸወ፡፡ ከእነዚህ መካከል የንጉሠ ነገሥቱ ሠራዊት የቦረንትቻ ባሕል ያውቅ እንደነበር በተክለጻዲቅ መኩሪያ መጻፉና ከዐጼ ልብነድንግል የጦር አዛዦች አንዱ የነበረው ቱሉ ደገልሀን በመራው ከኢማም አሕመድ ጋር የተካሄደ ጦርነት የዐጼው ጦር ሲያፈገፍግ ንጉሠ ነገሥቱ “ሁሉም ቢፈራ ቱሉ እንዴት ፈራ? ” ማለታቸው ስለሠራዊታቸው ሥብጥር የሚነግረን ነገር አለ፡፡

ኦቶማን ቱርኮችን እና የዘመኑ ተላላኪዎቻቸውን ለመዋጋት የንጉሠ ነገሥቱ ሠራዊት አንድ አካል ሆነው እስከ ኤርትራ ድረስ ዘምተው ስለነበሩ የኦሮሞ ተዋጊዎች ተጋድሎ የዐጼ ሠርጸድንግል(1542-1590 ዓ.ም.) ዜና መዋእል በግልጽ አስፍሯል፡፡ እነዚህ የኦሮሞና የሌሎች ሕዝቦች ተወላጅ ወታደሮች ትግራይ እንጢጮ አካባቢ ያካሄዱትን አውደ ውጊያ ዜና መዋዕሉ ይተርካል፡፡ ለመንግሥታቸውና ለሀገራቸው እስከባሕር ጠረፍ ድረስ ዘምተው ዋጋ መክፈላቸውም ተመዝግቧል፡፡ የዐጼ ሱስንዮስ(1607-1632 ዓ.ም.) ዜና መዋእል እና በዘመኑ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩ የአውሮፓ(የፖርቱጋል) ተጓዦች የጻፏቸው የመረጃ ምንጮች ንጉሠ ነገሥቱ ግንደበረት፣ሐምቦና አካባቢው ቤታቸው እንደነበር፤ አጎታቸው ለማሞ እንደሚባል፣ ወላጅ እናታቸው(ሐመልማል ወርቅ) የአዛዥ ኩሎ ልጅ የነበረች፤ የዚሁ የሐመልማል ወርቅ ጎሳ ተወላጅ የሆነ ቡኮ የተባለ ኦሮሞና ሠራዊቱ ለአባይ ቅርብ የሆነች ምዕራብ ሸዋ ላይ ዐጼ ሱስንዮስ ሲያገኙት የነበረውን ደስታና የፍቅሩን ጽናት ዜና መዋዕሉ ሳይሰስት ጽፎታል፡፡ ዐጼ ፋሲል(ከ1632 እስከ 1667 ዓ.ም.) አባቱ ሱስንዮስ እናቱ የወሎ ቃሉ ሰው(እቴጌ ሥልጣን ሞገሳ የሚል ስም የተሰጣት) እንደሆነች የታሪክ ምንጮች ያስረዱናል፡፡ በ1620ዎቹ ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ ይኖር የነበረው ፖርቱጋላዊ ቄስ ጄሮኒሞ ሎቦ ስለዐጼ ፋሲል እናትና ኦሮሞ ዘመዶቻቸው በአይን ምስክርነት የሚያውቀውን ጽፏል፡፡ የእቴጌ ሥልጣን ሞገሳ አያት ስለብዝሀ ሃይማኖት አስፈላጊነት የነበራቸውን ግልጽ ፖሊሲ ጭምር ሎቦ ዘግቦታል፡፡ የዐጼ በካፋ(1721-1730 ዓ.ም.) እና የዐጼ ኢዮአስ(1747-1761 ዓ.ም.) ጎንደር መቼም ለሕዝቦች ውህደትና ትስስር ጥሩ ማሳያ ነበረች፡፡ የየጁ ኦሮሞ ገዢ የነበረው የአሚቶ ሴት ልጅ ዝነኛዋ ውቢት ልጇ ዐጼ አዮአስ ነበር፡፡ ኢዮአስ ከኦሮሞ አጎቱ ከደጃች ሉቦ ጋር ሥልጣኑን በጎንደር እንዴት እንዳጸና፤ የቤተ መንግሥቱም የሥራ ቋንቋ አፋን ኦሮሞ እንደነበረ የንጉሠ ነገሥቱ ዜና መዋዕልና በጀምስ ብሩስ ቅጽ ሁለት መጽሀፍ የተመዘገቡ የታሪክ መረጃዎች ያስረዱናል፡፡

መነሻውን ወሎ በማድረግ ጎንደር ጸንቶ የኖረው የየጁ ሥርወ መንግሥት(ወረ ሼኮች) መሥራቾች የመርሳው አባ ጌትዬ፣ የልጃቸው ጓንጉል አባ ሴሩ እንዲሁም የልጅ ልጃቸው የራስ አሊ ጓንጉል(አሊ ትልቁ) ታሪክ በኢዮአስ ዜና መዋዕል፣ በጀምስ ብሩስ መጽሐፍና በሌሎች በርካታ ሰነዶች ታሪካቸው ተዘግቧል፡፡ በኋላ ላይ በሽፈራው በቀለ(ፕሮፌሰር) እና ሞላ ትኩዬ የቀረቡ ጥልቅ ጥናቶች ይህን እውነት በዝርዝር ያስረዱናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቃለ ምልልሳቸው እንደጠቀሱት የእነዚህ መሪዎች የፖለቲካ ጋብቻ ታሪክ የሚያሳየን በሄዱበት አገር ሁሉ የሕዝቦች ትሥሥር እና የፖለቲካ ጋብቻ የኖረ ታሪካችን እና የጉልበታችን ምንጭ እንደነበረ ነው፡፡ በዳግማዊ ዐጼ ቴዎድሮስ ዘመን የተጻፉ የታሪክ ሰነዶች የወሎዋ ገዢ ወርቂቱ ወዳጆ(የማመዶች ሥርወ መንግሥት መሪ የኢማም አሊ አባ ቡላ ባለቤት) ንጉሥ ምኒልክ ከመቅደላ እስር ቤት እንዲያመልጡ ያደረጉ፤ አጃቢ ሠራዊት አሰማርተው ምኒልክን እስከሸዋ የሸኙ እንደነበሩ በዋናነት ከጸሓፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ታሪከ ዘመን ዘ ዳግማዊ ምኒልክ ዜና መዋዕል እና በመቅደላ አምባ እስር ላይ የነበሩ አውሮፓውያን ከጻፏቸው መረጃዎች እንረዳለን፡፡

ሥልጣኔዎቻችን ሁሉ ተደምረን ያሳካናቸው እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቃለ ምልልሳቸው አንስተዋል፡፡ የዐድዋ ዘመቻና ድሉ ለዚህ አንዱ ማሳያ እንደሆነ ተጨባጭ የታሪክ ምንጮች ያስረዱናል፡፡ በ1888 ዓ.ም. ለዓድዋ ዘመቻ ከመላው ኢትዮጵያ የተመመው ሠረዊት ወፍላ ላይ የነበረው ሠልፍ የንጉሠ ነገሥቱ ዜና መዋዕል እንኳን እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ “የመኳንንቱ የጦር መሣሪያ፣ወርቁ፣ ጣፋ፣ ብሩ፣ ሙጣው፣ ጫሜው፣ ሎሚታውና ኩፊታው፣ ከሌቻው፣ ወርቅ ለምዱ እንደጸሐይ ሲያበራ ዋለ፡፡” እንደጸሐይ የበራውን ሕብረ ባሕልና ሕብረ ማንነት ትርክቶቻችን በልኩ አጉልተው ያውቃሉ?

ሸዋና አካባቢው(ወሎን ጨምሮ) እንደ አንድ ጂዞ ስትራቴጂ ሥፍራ የሕዝቦች ውህደትና ትስስር መሠረት ሆኖት የመልክዓ ምድር መገኛው ለግብርና እና ለውጭ ንግድ የተመቸ በመሆኑ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ውስጥ ቁልፍ ቦታ ይዞ መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቃለ ምልልሳቸው መግቢያ አስታውሰውናል፡፡ ሸዋና አካባቢው ከመንግሥታት ምስረታ ጋር በተገናኘ ከዘጠነኛው አንስቶ እስካሁን ያለው ረዥም የታሪክ ጉዞ በርግጥም ሊነገር፣ ሊተነተን የአደባባይ ትርክት አካል ሊደረግ የሚገባው እውነት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሸዋ ሡልጣኔት ምስረታ( እ.አ..አ.896 ዓ.ም.) እስከ ዓድዋ ድል(1888 ዓ.ም.) ሥላወሷቸው የአርጎባ(የወላስማ/ወሊ አስማ ሥርወ መንግሥት)፣ የአማራ(ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት)፣ ኦሮሞ(ቱለማው በተለይ)፣ወርጂ፣ ጉራጌ፣ ጋፋት፣ ወዘተ ሕዝቦች ትስስርም ይሁን የፖለቲካ ጋብቻ የተመለከተ ታሪክ ከበቂ በላይ የታሪክ ማስረጃ ምንጮች ቢኖሩንም በታሪክ ግርዶሹ ምክንያት የወል ትርክት አካል መሆን አልቻለም፡፡

ኤንሪኮ ቼሩሊ ከሐረር አግኝቶ ያሳተመው በአረብኛ የተጻፈው የሸዋ ሡልጣኔት ዜና መዋዕል እንደሚያመለክተው ሡልጣኔቱን እ.አ.አ. በ896/7 የመሰረቱት የማህዙሚ ጎሳ አባላት ናቸው፡፡ መንግሥታቸውም ከ9ኛው እስከ 13ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በተከታታይ በገዙ አሥራ አራት ሱልጣኖች እንደጸና የታሪክ መረጃ ምንጮች ያመለክታሉ፡፡ የሸዋ ሙስሊም ሡልጣኔቱ መቀመጫ ከተማ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምሥራቅ 70 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኝ ወለላ የተባለች ሥፍራ እንደነበረች የጆርጅ ደብሊው ቢ ሀንቲንግፎርድ(1989) ጥናት ያመለክታል፡፡ የማህዙሚ ሥርወ መንግሥት ከመጨረሻዎቹ መሪዎች አንዱ የነበረው ሡልጣን ድልመራህ ወርጂዎች የይኖሩበት በነበረው አካባቢ በ1270ዎቹ በነበረ የርስ በርስ ጦርነት ድል ሳይቀናው ሲቀር ሕይወቱን ለማትረፍ ዐጼ(የአማራ ገዥ?) እንደሄደ ይህው የአረብኛ ዜና መዋእል ያስረዳል፡፡ የማህዙሚዎች የሸዋ ሡልጣኔት የተተካው በዋናነት የአርጎባዎች አገር በሆነው ይፋት(ዊፋት) ላይ በወላስማዎች ነበር፡፡ ወላስማዎች ከአጎራባቾቻው ጋር እየተጋቡ፣ እየተስማሙም እየተጋጩም የይፋት ሡልጣኔትን ከ13ኛው እስከ 15ኛው ክፍለ ዘመን ከሸዋ እስከ ምሥራቃዊ የኢትዮጵያ ጠረፍ እንዳስተዳደሩ ስፍር ቁጥር የሌለው የሰነድ( የኢብን ካልዱን ተማሪ የነበረው አል ማቅሪዚ ጽሑፍ- ኪታብ አል ኢልማም)፣ የአርኪዮሎጂና የቃል መረጃ ምንጮች አሉ፡፡

መነሻውን ሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ወሎ ያደረገው የክርስቲያኑ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት በአካባቢው ያሉ ሕዝቦች ተዋህደው ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በጋራ የመሠረቱት እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ አማራዎች፤ አርጎባዎች፣ ወርጂዎች፣ ጋፋቶች፣ ጉራጌዎች እና ኦሮሞዎች፣ አፋሮች፣ ሐረሪዎች ወዘተ በዚህ የሸዋ መንግሥታት የተጽዕኖ ምህዳር(Orbit) ውስጥ እንደሚገኙ ዜና መዋእሎች፣ የሃይማኖት ሰነዶች፣ የአርኪዮሎጂ ማስረጃዎች ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የኖሩ የቃል መረጃ ምንጮች ያመለክታሉ፡፡ ለምሳሌ ታደሠ ታምራት(ፕሮፌሠር) ከ13ኛው እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን የቤተ ክርስቲያንና መንግሥትን ግንኙነት ታሪክ ባጠኑበት መጽሐፋቸው የገላንና ያያ ሰዎች ሸዋ ውስጥ በ13ኛው ክፍለ ዘመን በኦዳ ዛፍ (ኮቢል የሚባል ዋርካ) ሥር ሃይማኖታዊ ሥርዓት ይፈጽሙ እንደነበር ገድለ አቡነ ቀውስጦስን ጠቅሰው ጽፈዋል(ገጽ 184)፡፡ ሸዋ የባለ ብዙ ማንነት ሕዝቦች ሀገር ከመሆኗ ባሻገር በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች ላይ መረጃ የተወልን መነኩሴው አባ ባህሪይ እንደገለጸው “ሸዋ የመንግሥት ሀገር ነች” (ገጽ 130)፡፡ በየዘመናቱ ከሸዋ የተነሱ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ፈረሰኛ ሠራዊታቸውን ይዘው በሰሜን እስከ ኤርትራ(በዐጼ ሠርጸ ድንግል ዘመን- የኤርትራዋ ባሬንቱ የዚህ የታሪክ ሂደት ውርስ አይደለችም ማለት አይቻልም፡፡) በምሥራቅ እስከ ዘይላ(ከዐጼ አምደጽዮን እስከ ገላውዲዮስ ዘመን)፣ በምዕራብ እስከ ሱዳን ፋዞግሊ(ዐጼ ሱስንዮስ ዘመን) በደቡብ እስከ ሞያሌ ተንቀሳቅሰው በአገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ተጫተዋል፡፡

እነዚህ የሸዋ እና አካባቢው ሕዝቦችና ገዢዎች ትልቁን ንቅናቄያቸውን ያደረጉት ግን በ19ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዐጼ ምኒልክና ራስ ጎበና ዳጬ የቱለማ ኦሮሞ፤ የሸዋ አማራ እና የሌሎችም ውህድ የሆነ ጦራቸውን አዝምተው ወሎ ወግተው ወረኢሉን የመንሥታቸው መቀመጫ ያደረጉት አርሲ፣ወለጋ፣ከሐረር ከመዝመታቸው በፊት ነበር፡፡ የመጫ ኦሮሞ ተወላጁን የጎጃሙን ንጉስ ተክለሃይማኖት(አዳል ተሰማ) በቱለማው መሪ ራስ ጎበና ዳጪ እምባቦ ላይ ያስገበሩት የጂኦ ፖለቲካዊ እና የሕዝቦች ትስስር እድሎች ጉልበት ፈጥሮላቸው፤ ኃይል አጎናጽፏቸው እንጂ በአጋጣሚ አይደለም፡፡ በርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖለቲካችን ደንቃራነት የፈጠረውን የታሪክ ግርዶሽ ያሸነፉ ፋና ወጊ ጥናቾች መውጣት ጀምረዋል፡፡ አንዱ “Invisible Actors: The Oromo and the Creation of Modern Ethiopia(1855-1913)” በሚል ርዕስ በብሪያን ጀምስ ዬትስ(2002) በኤሊኖይስ ዩኒቨርሲቲ ከተጠናው እጅግ ጠቃሚ የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጥናት ሲሆን ሌላው የደቻሳ አበበ(ዶ/ር) ጎበና ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቃለ ምልልሳቸው የዘመናዊት ኢትዮጵያን እውን መሆን ያለ ምኒልክና ያለ ጎበና እንደማይታሰብ ሲጠቅሱ ይህንን እውነታ ማጉላታቸው ይመስለኛል፡፡

የሕዝቦች ትስስርና የፖለቲካ ጋብቻ በአማራና በኦሮሞ ሕዝብ መስተጋብር ብቻ የታጠረ አልነበረም-ሊሆንም አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባህልና ሥልጣኔ መጋመዱ ረቂቅ ነው፡፡ ከጥንታዊ አክሱም ዘመን ጀምሮ በዝነኞቹ የአክሱም መቃብር ሀውልቶች እና በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ ከምናገኛቸው የኪነ ሕንጻ ትእምርቶች(Symbols) መካከል የውሸት በሮች (False Doors) እና የውሸት መስኮቶች(False windows) የሙታን መንፈስ(ኤከራ) መመላለሻ እንደሆኑ በጥናት የተረጋገጠ ነው (ቢትራይስ ፕሌይን Annales d’Éthiopie 1965) ፡፡ ይህ የኤከራዎች መመላለስና የመነጋገር ባህል እና እምነት ከደቡባዊ ግብጽ አንስቶ እስከ ሰሜን ኬንያ ድረስ በሚኖሩ የኩሽ ሕዝቦች በሰፊው የሚታወቅ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ልምምድ ነው፡፡

ሌላው በልኩ ያልተጠና እና በትርክቶቻችን ውስጥ ትኩረት ያልተሰጠው በሕዝቦች መካከል ያለ ሥልጣኔ ትስስር ታሪክ የእያንዳዱን የዛግዌ ነገሥታት የሥልጣን ዘመናትን የተመለከተ ነው፡፡ ከታሪክ ነገሥት፣ ከልዩ ልዩ ዜና መዋዕሎች፣ ከፖርቱጋል ተጓዦች(ፓኤዝና አልሜዳ) ከብሪቲሽ ሙዝየም እንዲሁም ከኮንቲ ሮሲኒ የተገኙት ምንጮች የሚረጋግጡት የሁሉም የዛግዌ ዐጼዎች( ከአንድ ሁለቱ በስተቀር) የሥልጣን ዘመን 40፤40 ዓመታት ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ በኦሮሞ የገዳ ሥርዓት የአንድ ትውልድ የሥልጣን ዑደት ጋር አንድ አይነት የሆነው በአጋጣሚ ነው ወይስ ዛግዌዎች እና ኦሮሞዎች የኩሽ ሕዝቦች በመሆናቸው ቀዳሚ ከሆነው የጋራ ሥልጣኔያቸው የሚቀዳ የአስተዳደር ሥርዓት ነው? እነዚህስ ሀቆች የወል ትርክቶቻችን መመሆን አለመቻላቸው በፖለቲካ ደንቃራነት የተፈጠረ የታሪክ ግርዶሽ(eclipse of history) እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል? በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትና እና በሸዋ በሚገኘው የአዳዲ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ኪነሕንጻ መካከል ያለው ፍጹም ተመሳሳይነት ምንጩ ምንድነው? ሊጠና፣ ሊነገር ልንማርበት ይገባል፡፡

በርግጥም ታሪካችን ትዝታችን ላይ የተጫነ ሸክም ሳይሆን የነፍስ መገለጥ ነው የሚያሰኘው የሕዝቦች ትሥሥር፣ ውህደት የሥልጣኔ መጋራትና መወራረስ ታሪክ መታወቁ መንፈስን ሃርነት ማውጣቱ ይመስለኛል፡፡


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2