የሴዶ እና የጆኒ ታላቅ የMMA ፍልሚያ ነሐሴ 21 ይካሄዳል!

- Advertisement -
Sidebar AD

#Fastmereja:-በኢትዮጵያ የማርሻል አርትስ እና የቦክስ ስፖርት ታሪክ ያልተነካውን እምቅ አቅም ለዓለም ለማሳየትና ስፖርቱን ለወጣቶች የቋሚ ገቢ ምንጭ ለማድረግ ያለመው ”አድዋ ፋይት ናይት 2″ (ETFC 002) ታላቅ የውድድር ምሽት ነሀሴ 21 እንደሚካሄድ በዛሬዉ እለት ተገለፀ።

ነሀሴ 21 በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ በስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ ከፍተኛ ትኩረትን የሳበው እና በጉጉት የሚጠበቀው ዋና ፍልሚያ (Main Event) በጆኒ (Johnny) እና በሴዶ (Sedo) መካከል የሚደረገው ድብልቅ ማርሻል አርት (MMA) ግጥሚያ እንደሆነ ተገልጿል።

ዛሬ በተሰጠው የጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተወዳዳሪዎች በፊት ለፊት ፍጥጫ (Face-to face) የተገናኙ ሲሆን እርስ በእርስ ያቀረቧቸው የተፎካካሪነት እና የስነ-ልቦና የበላይነት የመውሰጃ አስተያየቶች በስፍራው የነበረውን ስሜት ያጋገሉት ሲሆን፣ ሁለቱም ስፖርተኞች ለነሐሴ 21ዱ ታላቅ ፍልሚያ ያላቸውን ከፍተኛ ዝግጁነትና የማሸነፍ በራስ መተማመን አሳይተዋል።

የውድድሩ አዘጋጅና የስዊት ቦክስ መስራች እና ስራ አ አቶ ጌታቸው መለሰ በበኩላቸው፣ ETFC 002 የቀደመው ETFC 001 ከተካሄደበት ፍጥነትና ሁኔታ በተሻለ መልኩ በከፍተኛ ደረጃ ተዘጋጅቶ የቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

አዘጋጆቹ ለፕሮግራሙ መዘገየት ይቅርታ በመጠየቅ፣በተወዳዳሪዎቹ የስነ-ምግባር ጥንካሬ ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸውና ስፖርተኞቹ ሀገራቸውን በዓለም አቀፍ መድረክ ማስጠራት የሚችሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በምሽቱ 11 የተመረጡ ፍልሚያዎች የሚካሄዱ ሲሆን፣ 4 የቦክስ (Boxing) 4 የኤምኤምኤ (MMA) 3 የሙአይ ታይ (Muay Thai) ፍልሚያዎች ናቸው።

በዝግጅቱ ላይ የሴቶች ተሳትፎ ልዩ ቦታ የተሰጠው ሲሆን፣ አትሌት አብስላት እና ዛራ በተወዳዳሪነት የሚሳተፉ ሲሆን በቀጣዩ «አድዋ ፋይት ናይት 003» ውድድር ላይ ደግሞ የሴት ተወዳዳሪዎች ቁጥር እንዲጨምርና ሰፊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል፣ በቀደሙት ዝግጅቶች የነበረውን የመቀመጫ መደራረብ ችግር ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ የተሰራ ሲሆን በዚህም ተመልካቾች ትኬት በሚቆርጡበት ወቅት ቀጥታ የመቀመጫ ቦታቸውን (Seat) መርጠው እንዲይዙ እንደሚደረግም ነዉ የተገለፀዉ።

አዘጋጆቹ እንዳብራሩት፣ በቅርቡ በሚካሄዱት ETFC-003 እና ETFC-004 የውድድር መድረኮች ላይ የሀገር ውስጥ ስፖርተኞች ከውጭ ሀገር ተወዳዳሪዎች ጋር እንዲጋጠሙ እንደሚደረግ የተገለፀ ሲሆን ይህም በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ እንደ ኡሲክ (Usyk) ያሉ ታዋቂ የዓለም አቀፍ ቦክስ ውድድሮችን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማዘጋጀት ለተያዘው ታላቅ ዕቅድ መንገድ የሚከፍት ነው ተብሏል።

ይህ ዝግጅት በአድዋ ድል መታሰቢያ፣ በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ የስፖርት አመራሮች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች አስተዋጽኦ የሚካሄድ ሲሆን፣ የስፖርት አፍቃሪያን የነሐሴ 21ዱን የሴዶ እና ጆኒ ፍልሚያ በከፍተኛ ጉጉት በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ።

📷 ከበደ መክብብ






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2