ቀብር

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅነትና በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ከ40 ዓመታት በላይ በኃላፊነት ሲሠሩ የነበሩት ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው አረፉ።

ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው በ83 ዓመታቸው ያረፉት ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም. በአጋጠማቸው ድንገተኛ ሕመም ነው።

​ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው ሴቶች ከዩኒቨርሲቲ ለመመረቅና በከፍተኛ ኃላፊነት ተመድበው ለመሥራት ብርቅ በነበረበት ጊዜ በውጤት ያለፉ፣ በፋና ወጊነት በሚቆጠር አርአያነት፣ በከፍተኛ ተሳትፎ ሀገራቸውን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

​በ1950ዎቹ መጨረሻ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፣ ከዋሺንግተን ዲሲ አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለወጣት ሴቶች ምሳሌ ለመሆን የበቁ ነበሩ።

​ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው ከ40 ዓመታት በላይ በኃላፊነትና በሥራ መሪነት ባገለገሉባቸው የግልና የመንግሥት መስሪያ ቤቶች አዳዲስ የሥራ ዘዴዎችን በመቀየስና የተቀናጀ አሠራር በማስለመድ ስማቸው በመልካም ሲጠራ ቆይቷል።

​በተለይም ለ19 ዓመታት በዋና ሥራ አስኪያጅነት የመሩትን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ትርፋማ ለማድረግ፣ አሠራሩን ለማዘመንና ጠንካራ ተቋም እንዲሆን ያበረከቱት አስተዋጽኦ በጊዜው በነበሩትና ሰነድ በሚመረምሩት ዘንድ የታወቀ ነው።

እንደ ፈጣን ሎተሪ ዓይነቶቹ ከጊዜው ጋር የተጣጣሙ አሠራሮች በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር እንዲለመዱና የተጠናከሩ እንዲሆኑ ያደረጉት ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው ናቸው።

​በኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ በኅብረት ኢንሹራንስ፣ በናይል ኢንሹራንስ፣ በብርሃን ኢንሹራንስ በመመሪያ ሥራ አስኪያጅነት እየተመደቡ ተቋሞቹ እንዲጠናከሩ ሙሉ ልምዳቸውንና ችሎታቸውን ማስተላለፋቸውን አብረዋቸው የሠሩት እየመሰከሩላቸው ነው።

​ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው ትኩረትና ጥንቃቄ ከሚጠይቀው የሥራ መደባቸው ጋር ደርበው እንደ ቤተሰብ መመሪያ ማኅበር ከአንዴም ሁለቴ፣ እንደ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ እንደ ኢየሩሳሌም የሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅትና በመሣሰሉት ተቋማት ለረጅም ዓመታት በቦርድ ሊቀ መንበርነትና አባልነት፣ በሥራ አስፈጻሚነትም ጭምር ሲሠሩ ቆይተዋል።

​ዘለግ ላለውና ውጤታማ ለሆነ ሥራቸው የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል።

እስከ ሕልፈታቸው ድረስ ከሥራ ሳይለዩ በጥናትና በምርምር ሥር ቆይተዋል።

​የሁለት ልጆች የሆኑት ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው የቀብር ሥነ ሥርዓት ኮተቤ በሚገኘው በመካነ ቅዱሳን ሐና ወኢያቄም ቤተ ክርስቲያን ሐሙስ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ከቀኑ በ6:00 ሰዓት እንደሚፈጸም ቤተሰቦቻቸው ነግረውናል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)





Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2