የቤተ-እስራኤላውያንን ህይወት እና ስውር ታሪክ የሚያወሳው “ከምኩራቡ በስተጀርባ” የተሰኘው አዲስ መጽሐፍ በስቴይ ኢዚ ፕላዛ በድምቀት ተመርቋል።
በደራሲ ዶክተር ኢዮስያስ እሱንዳለ የተሰናዳው ይህ አጓጊ ሥራ፣ በኢትዮጵያ ማህበራዊ ታሪክ ውስጥ “ባለእጆች” እየተባሉ የሚጠሩትን የቤተ-እስራኤላውያን ማህበረሰብ ሕይወት፣ የደረሰባቸውን ማህበራዊ ጫና እና የማንነት ጥያቄ በልብ-ወለድ መዋቅር ውስጥ ፈትሾ ያቀርባል።
መጽሐፉ ደራሲው በዶክትሬት (PhD) ጥናታቸው ላይ ተመርኩዘው ያዘጋጁት ሲሆን፣ ታሪኩ ከአዲስ አበባው ቀጨኔ እና ጉለሌ ሰፈሮች ተነስቶ እስከ መርሃቤቴ ይዘልቃል። በዘመናዊ እውቀት የሰለጠነው አባተ የተባለ ወጣት ምሁር የሚያደርገውን ውስጣዊ የማንነት ፍለጋ፣ የቀጨኔን ምኩራብ አምልኮ እና የታሪካዊውን “ዘመቻ ሙሴ” ምስጢራዊ የስደት ውጣ ውረዶች በከፍተኛ የታሪክ መረጃዎች አስደግፎ አቅፏል።
በምርቃቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ ደራሲው የወላጆቻቸውን የ55 ዓመት የጋብቻ ዘመን በካባ በማልበስ ያከበሩ ሲሆን፣ መጽሐፉም የአባ ቢተውና የባለቤታቸውን የ60 ዓመታት የትዳር ጽናት፣ ባህላዊ የዕራት ማዕድ ሥርዓት እና ጠንካራ የማህበረሰብ እሴቶችን ያጎላል። በተጨማሪም አባተ ከአውቶብስ ጉዞ ላይ ከተዋወቃት «ሰላም» ከተባለች ነርስ ጋር ያሳለፈውን ጥልቅ የፍቅር ታሪክ አካቷል።
የመጽሐፉ የቋንቋ አማካሪ ዶክተር ዘላለም ግርማ እንደገለጹት፤ ሥራው የቆየውን የአዲስ አበባ ሰፈር ድባብ እና ህያው የቋንቋ ዘይቤ በከፍተኛ ጥራት የጠበቀ፣ የፍትህ፣ የፍቅርና የጽናት መገለጫ የሆነ የታሪክ ሀብት ነው። መጽሐፉ እንደ «ፈ ላሻ» እና «ካይላ” ያሉ ስሞች ለዘመናት እንዴት እንደ ስ ድብ ያገለግሉ እንደነበር በመተንተን፣ በማህበረሰቡ ላይ የደረሰውን የስነ-ልቦና ጠባሳ በግልጽ ያወጣል።
በምርቃት መርሃ-ግብሩ ላይ ለማህበረሰቡ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ታዋቂ ግለሰቦች የተገኙ ሲሆን፣ ከእነሱም መካከል ደራሲና ገጣሚ ከፈለኝ ዘለለው፣ መጋቢ ዶክተር ሰለሺ ከበደ፣ የህክምና ድጋፍ አስተባባሪዋ ወ/ሮ ዘነበች እና የማህበረሰብ ተወካዩ አባ እሸቱ ይገኙበታል። እንዲሁም በልማት ስራዎች የተሰማሩት አቶ ሰለሞን አሰፋ፣ መጋቢ ደምስ ማሞ እና የሰሊሆም ድርጅት መስራች ወጣት ሚኪያስ ለገሰ ታድመዋል።
የጽሑፉ ገምጋሚዎች እንዳመለከቱት፣ መጽሐፉ እውነተኛ ታሪክን ከልብ ወለድ ትረካ ጋር አዋህዶ ማቀረቡ ለአንባቢው ሳቢና ቀልብ ገዢ ያደርገዋል። ፀሐፊው በማህበረሰባዊ መገለልና በማንነት ክፍፍል ላይ የነበረውን አመለካከት በመቃወም፣ በእውቀት እና በጽናት ላይ የተመሰረተ ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን ጥሪ ያቀርባል።
በአጠቃላይ “ከምኩራቡ በስተጀርባ” መጽሐፍ ለዘመናት ተሸፍነው የቆዩ ታሪካዊ እውነታዎችን፣ የስደት ጉዞዎችን እና የማህበረሰቡን ሃይማኖታዊና ባህላዊ አደራ ለትውልድ የሚያስተላልፍ ውድ ቅርጽ ሆኖ ለአንባቢያን ተበርክቷል።
Source: FastMereja









No comments yet.