ሩስያ በኪየቭ ላይ የከፈተችው ከባድ ጥቃት 17 ሰዎችን ገደለ፤ ዩክሬን የአየር መከላከያ እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ደረሰ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ሩስያ ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭና በአካባቢዋ ላይ ከፈተችው መጠነ ሰፊ የሚሳይልና የድሮን ጥቃት ቢያንስ 17 ሰዎች ሲገደሉ 44 ያህል ሰዎች ቆስለዋል። ጥቃቱ በ2026 በኪየቭ ላይ ከተፈጸሙት ከባድ ጥቃቶች አንዱ መሆኑን ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ዘግበዋል።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ እንዳሉት፣ ሩስያ 24 የኢስካንደር-ኤም ባሊስቲክ ሚሳይሎች፣ ሌሎች 4 ረጅም ርቀት ሚሳይሎች እና 115 የሻሄድ ድሮኖችን ተጠቅማ ጥቃቱን ፈጽማለች።

የዩክሬን አየር ኃይል 98 ድሮኖችን መትቶ መጣሉን ቢያስታውቅም፣ ወደ ኪየቭ የተተኮሱትን ባሊስቲክ ሚሳይሎች ግን አንዱንም ማምከን አልቻለም።

የጥቃቱ ዋና ኢላማዎች የሲቪል መጋዘኖች፣ የሎጂስቲክስ ማዕከላት፣ የባቡር ጣቢያዎች እና የንግድ ተቋማት እንደነበሩ ተገልጿል።

በጥቃቱ የ20 ፎቅ የመኖሪያ ሕንፃ፣ ትላልቅ መጋዘኖች እና የንግድ ማዕከላት ወድመዋል፤ በብዙ ቦታዎች ከባድ እሳት ተነስቶ የማዳን ሥራዎች ለሰዓታት ቀጥለዋል። በኪየቭ ቢያንስ ሰባት ወረዳዎች ውስጥ ጉዳት መድረሱም ተረጋግጧል።

ይህ ጥቃት ዩክሬን ያለባትን የአየር መከላከያ ችግር በድጋሚ አጉልቶ አሳይቷል። የባሊስቲክ ሚሳይሎችን በብቃት ማምከን የሚችሉት የፓትሪዮት መከላከያ ሥርዓቶች እጥረት በመኖሩ የተነሳ ሚሳይሎቹ ወደ ኢላማቸው መድረሳቸውን የምዕራባውያን ሚዲያዎች ጠቁመዋል።

ዜሌንስኪ ለምዕራባውያን አጋሮች ያቀረቡትን ጥሪ በድጋሚ በማደስ፣ “የባሊስቲክ ሚሳይል መከላከያ ሥርዓቶች በጊዜው ቢደርሱ ብዙ ሕይወቶች ሊድኑ ይችሉ ነበር” ብለው ተጨማሪ የፓትሪዮት ሥርዓቶችና ሚሳይሎች እንዲላኩ ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ ጊዜ ዩክሬንም በሩስያ ውስጥ የሚገኙ የሎጂስቲክስ እና የኢንዱስትሪ ተቋማትን በረጅም ርቀት ድሮኖች ማጥቃቷን ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ የሁለቱ ሀገራት የተቃጣጠለው ጦርነት አሁንም የመቀዛቀዝ ምልክት አላሳየም።

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ላየን፣ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ መሪዎች በሲቪል ተቋማት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በማውገዝ ዩክሬን ተጨማሪ የአየር መከላከያ ድጋፍ እንዲያገኝ ጥሪ አቅርበዋል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)



Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2