#Ethiopia | የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ፣ በመዲናዋ በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የግብር ጫና እንዳይጨምርባቸው፣ ተግባራቸው እንዲጠናከርና ወደ ቀጣይ የንግድ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ለማስቻል በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
ቢሮው በሰጠው መግለጫ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ፍትሐዊ የግብር አሰባሰብ ስርዓት ለመዘርጋት፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ የመልካም አስተዳደርን ለማጠናከር እና የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል ሰፋፊ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቋል።
ለ2018 የግብር ዘመን በአዲስ አበባ 456 ሺህ 433 የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች እንደሚገኙ ጠቅሶ፣ ከእነዚህ 9.2 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጿል። አብዛኞቹ ግብር ከፋዮችም በኦንላይን ስርዓት ግብራቸውን እየከፈሉ መሆኑን አመልክቷል።
ቢሮው እንደገለጸው፣ የደረጃ “ለ” ነጋዴዎች የሚከፍሉት ግብር ከተቀጣሪ ሰራተኞች ግብር ያነሰ ሲሆን፣ ይህም አነስተኛ ነጋዴዎችን ለማበረታታትና ለማሳደግ የተወሰደ ፖሊሲ መሆኑን ገልጿል።
እስከ ሐምሌ 25 ድረስ የክፍያ መልዕክት የደረሳቸው ግብር ከፋዮች እስከ ሐምሌ 30 2018 ዓ.ም. ድረስ በኦንላይን እንዲከፍሉ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ መልዕክቱ ያልደረሳቸው ወይም ከሐምሌ 25 በኋላ የደረሳቸው ደግሞ ያለ ቅጣት እስከ ነሐሴ 20 2018 ዓ.ም. ድረስ መክፈል እንደሚችሉ ገልጿል።
በተጨማሪም፣ “ግብር በዛብኝ” የሚል ቅሬታ ላላቸው ግብር ከፋዮች የቅሬታ አፈታት ስርዓት ወደ ስራ መግባቱን ጠቁሞ፣ በስልክ የተላከው የዓመታዊ ግብር መጠንም ቀደም ሲል የተከፈለውን ቅድመ ታክስ ተቀናሽ በማድረግ መሰላቱን አስረድቷል።
በሌላ በኩል፣ በ2019 በጀት ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ 502.27 ቢሊዮን ብር በጀት ያፀደቀች ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 380 ቢሊዮን ብር ገቢ በፍትሐዊነት ለመሰብሰብ በገቢዎች ቢሮ መታቀዱን መግለጫው አስታውቋል።
Source: GetuTemesgen









No comments yet.