አባቢያ 11ኛ ዓመቱን አክብሯል!

- Advertisement -
Sidebar AD

ሻማዎቹ በርተው፤ ፊቱም በልጅነት ደስታው ተሞልቶ ይሆናል። ከደስታው ጀርባ የማይበራ አንድ ቦታ ግን አለ፤ የአባቱ ቦታ!

ዛሬ አባቱ መቶ አለቃ ጌታቸው መሮዳ ከጎኑ የሌለው ጦርነት በፈጠረው ቀውስ ሳቢያ ነው። አባቱ አባቢያን ትከሻው ላይ እንደተሸከመው አብሮት በበረሃ ታግቶ ነበር። ለልጁ ሲል መራራ መከራንም ቀምሶ ነበር። በመጨረሻም ልጁን ትቶልን በዛው ጦርነት ነፍሱን ተነጥቋል።

አባቢያ ግን [እግዚአብሔር ይመስገን] የ11ኛ አመት ልደቱን አከበረ። በህይወት አለና! ምናልባት የዚህ ልደት ትልቁ ትርጉምም ይሄ ይሆናል፤ ከጦርነት በኋላ መኖር ራሱ ድል ነው።

የቀድሞው ቁስል ሳያጠግግ፣ እንባ ሳይደርቅ፣ የሞቱ/የጠፉ ሰዎች ትዝታ ሳይርቅ፤ እንደገና በሌላ ጦርነት…!

ለምን?

ጦርነት የሚጀምረው በቃላት ነው፤ የሚጠናቀቀው ግን በቀብር ነው። መሐሉን የሚሞሉት ደግሞ የእናቶች እንባ፣ የልጆች ጥያቄ እና የቤተሰብና ሀገር ባዶነት ነው።

አባቢያ አንድ ነገር ሊያስታውሰን ይገባል። ጦርነት ለአዋቂዎች የታሪክ አንድ ምዕራፍ ሊሆን ይችላል፤ ለልጅ ግን የልጅነቱ የባከነ/የጠፋ ክፍል ነው። አንድ ልጅ አባቱ በጦርነት ቢሳተፍ እንኳ አባቱ በድል ወይም በሽንፈት መሆኑ ሳይሆን በህይወት ውደ ቤቱ እንዲመለስ ነው የሚፈልገው። የጦርነት ድል ወይም ሽንፈት ለእሱ ሁለተኛ ነገር ነው!

የአባቢያን 11ኛ ልደት በሻማ ብቻ አናክብረው። በምርጫችንም እናክብረው። ሌላ ልጅ አባቱን እንዳያጣ፣ ሌላ እናት ልጇን እንዳትቀብር፣ ሌላ ቤት ወንበሩ ባዶ እንዳይቀር። የጦርነትን ዋጋ የሚከፍለው ጦርነቱን የሚቀሰቅሰው ወይም የሚያወራው አካል ብቻ አይደለም፤ ትውልድም ጭምር እንጂ!

ለጦርነት ሁሌም እንዘግይ! ጦርነት አሸናፊ እንኳን ቢኖረው፣ ልጆች ሲያለቅሱ ድል አይሆንም።

ሰላም ለሃገሬ!
ጋዜጠኛ ሶዶ ለማ





Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2