ወደ ቤተ መቅደስ ገባች🙏🙏🙏
በመካንነት የነበሩት ወላጆቿ ኢያቄምና ሐና በንጽህና በቅድስና ቢኖሩም በወቅቱ የነበሩት ካሕናተ ኦሪት ልጅ ስላልወለዱ መስዋዕታቸውን እንኳን ሊቀበሏቸው ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡
ወላጆቿ ወደ እግዚአብሔር ጸልየው፣ ልጅ ከሰጣቸው ለቤተ እግዚአብሔር ሊሰጡ ስዕለት ገብተው ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለዱ፡፡ እመቤታችን ገና በቅድስት ሐና ማሕጸን ከነበረችበት ወቅት ጀምሮ ተአምራት ታደርግ ነበር፡፡ ቤርሳቤህ የተባለች ሴት የሀናን መጽነስ ስትሰማ በደስታ ልትጎበኛት መጣች፡፡ አንድ አይኗን አጥታ የነበረችው ይህች ሴት ቅድስት ሐናን እንኳን ደስ አለሽ ብላ ሆዷን ከዳሰሰቻት በኋላ በዚያው እጇ ዓይኗን ብትነካው ዐይኗ በርቶላታል፡፡
ይህን ምሳሌ አደርገው ድውያን እየመጡ ሆዷን ዳሰው ይፈወሱ ነበር፡፡ በቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ ወላጆቿ ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሀና ፍሬ አጊኝተዋል፡፡ ዓለም ደግሞ የመድኃኒቱን እናት አጊኝቷል፡፡
እናታችን ቅድስት ሐና እመቤታችን ጸንሳ ሳለች ሳሚናስ የሚባል የአጓቷ ልጅ ይሞታል፡፡ ቅድስት ሐናም እጅግ ትወደው የአልጋውን ሸንኮር እየዞረች ስታለቅስ ከሞተበት ተነስቶ “የሰማይና የምድር ፈጣሪ አያት ሆይ ላንቺ ክብር ይገባሻል!!!” ብሎ መስክሮ አርፏል፡፡ አይሁድም “ቀድሞ የእነዚህ ዘር የነበሩ ዳዊትና ሰሎሞን አርባ፣ አርባ ዘመን ገዙን አሁን ከዚህች የሚወለድ ምን ሊያደርገን ነው?” ብለው በድንጋይ ሊወግሯት ተነሱ፡፡ የራማው ልዑል ቅዱሰ ገብርኤል እየመራ ወደ ሊባኖስ ተራራ ወሰዳቸው፡፡ በእዚያም ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች፡፡ ሰማያት ብርሃን ሰጡ፣ ቅዱሳን መላእክት አዲስ ምስጋና ተቀኙላቸው፣ የሊባኖስ ተራራም በብርሃን ደመቀ፡፡ በጨለማውስጥ የነበረው ዓለም ብርሃን የሚያይባት፣ የእውነተኛው ጸሐይ እናቱ ተወለደች፡፡ አባቷ ንጉስ ሰሎሞን “ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ” እንዳለ በሊባኖስ ተራራ ተወለደች፡፡
ኢያቄምና ሐና የተሳሉትን ስእለታቸው አስታውሰው በሦት ዓመቷ ወስደው ለቤተ እግዚአብሔር ሲሰጧትም ካህኑ ዘካርያስ ስለምግቧ ስለተጨነቀ፤ ሕዝቡን ሰብስቦ ሳለ መልአኩ ፋኑኤል ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ይዞ ከሰማይ ወረደ፤ ዘካርያስ ለእርሱ የመጣ ሀብት መስሎት ሊቀበል ሲቀርብ ወደ ላይ ራቀበት፡፡ ከእርሱ በታች ካለው ስምዖን ጀምሮ በዚያ የተሰበሰቡት ሰዎችም በየተራ ቢሞክሩ በተመሳሳይ መልኩ ወደ ላይ ራቀባቸው፡፡ ምን አልባት ለእንግዶች የመጣ ሀብት እንደሆነ ብለው ሐናና ኢያቄም እንዲቀርቡ አደረጓቸው፤ ነገር ግን ለእነርሱም ራቀባቸው፤ ዘካርያስም ሐናን “እግዚአብሔር የሚያደርገውን የሚያውቅ የለምና ልጅቷን ትተሸ ወደዚህ ነይ” አላት፤ በዚያም ጊዜ ቅድስት ማርያም እናቷን ስትከተል መልአኩ ፋኑኤል ፈጥኖ ወርዶ አንድ ክንፉን አንጥፎ አንድ ክንፉን ጋርዶ መግቧት፤ በክብር ዐረገ፡፡
ሊቀ ካህናቱና ሕዝቡም “የምግቧ ነገር ከተያዘልን በቤት እግዚአብሔር ትኑር” ብለው ታህሣስ 3 ቀን ወደ ቤተ መቅደስ አስገቧት፡፡ ለ12 ዓመታትም ሰማያዊ ኅብስትና መጠጥ እየተመገበች በቤተ መቅደስ ኖረች፡፡ በ15 ዓመቷም ለአቅመ ሔዋን በመድረሷ ከቤተ መቅደስ ትውጣልን በማለት አይሁድ በጠላትነት ተነሡባት፡፡ ካህኑ ዘካርያስም በጸለየ ጊዜ እግዚአብሔር አረጋዊው ዮሴፍ እንዲጠብቃት ምልክትን ሰጣቸው፡፡ ርግብም መጥታ በራሱ ላይ ዐረፈች፤ ስለሆነም ዮሴፍ እንዲጠብቃት ተወሰነ፡፡ ቤተ መቅደስም እየተመላለሰች ታገለግል ነበር፡፡
በመልአኩ ብስራትም የዓለሙ መድኅን ጌታን ጸንሳለች፡፡ ይህችን ብርሃን፣ የብርሃን እናት ገዳማውያን አባቶችና እናቶች ዘወትር በጸሎታቸው ያስቧታል፡፡ ገዳማቸውን እናግዝ፣ በዓታቸውን እናጽና፡፡
ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391
ወይም
አቢሲኒያ ባንክ
141029444
ለበለጠ መረጃ:- 09 38 64 44 44/0918077957
Source: Yeneta Tube









No comments yet.