*ፍሰሐ ወልደአማኑኤል ማነው?
(ከዕዝራ እጅጉ)
#Ethiopia | አቶ ፍሰሐ ወልደ አማኑኤል፣ ከአባታቸው በጅሮንድ ወልደ አማኑኤል ደምሴ እና ከእናታቸው ወይዘሮ አየለች በሻህ በሐረር ልዩ ስሙ “ደደር” በሚባል አካባቢ በሰኔ 1941 ዓ.ም ተወለዱ። ለቤተሰባቸውም 4ኛ ልጅ ናቸው።
አቶ ፍሰሐ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል በራስ መኮንን የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ተምረው ከ6ኛ እስከ 10ኛ ክፍል አዲስ አበባ መጥተው በዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
በታዳጊነታቸው እግርኳስ የሚወዱት አቶ ፍስሐ ህልማቸውም ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋች መሆን ነበር። አባታቸው ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ይመክሯቸውም ነበር።
የመጀመሪያ የአዲስ አበባ ክለባቸው መኩሪያ(ክብር ዘበኛ) ሲሆን ቀጥለውም በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ለ9 ዓመታት ያህል ተጫውተዋል።
ፍሰሐ ወ/አማኑኤል፣ ሀገራቸውን በ4 የአፍሪካ ዋንጫ በመወከል የተሳተፉ ሲሆን ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው በ6ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ 9 ቁጥር ለብሰው ያሳዩት ብቃት በኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ምንጊዜም የማይረሳ ነው።
በ1961 ባገኙት ነፃ የትምህርት ዕድል ምክንያት ወደ አሜሪካ ሀገር ያቀኑት ፍሰሀ ወ/አማኑኤል የካሊፎኒያ ሎስአንጀለስ ዩኒቨርሰቲ ተቀላቀሉ። በፖለቲካ ሳይንስም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ።
በዩኒቨርስቲው በሚማሩበት ወቅት በእግር ኳስ ተጫዋችነት አገልግሎት ሰጥተዋል።
በመቀጠልም፣ የአይሁዳውያን ክለብ ለሆነው “ለማኪብ” ክለብ ተጫውተዋል። በጊዜውም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በፓለቲካ ሳይንስ ተምረው ማጠናቀቅ ችለዋል።
አቶ ፍሰሀ ወ/አማኑኤል ከማኪባ የእግርኳስ ክለብ በመልቀቅ ታዋቂውን የሎስአጀንለስ አቴክስ ክለብ የተቀላቀሉ ሲሆን በክለቡ ቆይታቸውም ከማንችስተሩ ታዋቂ ተጫዋች ጆርጅ ቤስት ጋር እንዲሁም ከፔሌ ጋር አብረው ተጫውተዋል። በክለቡም ውስጥ ታሪክ የማይዘነጋውን ውለታ መዋል ችለዋል።
ፍሰሀ ወ/አማኑኤል በአሜሪካ ሀገር የሰሜን አሜሪካ የእግር ኳስ ፌዴረሽን ከዛሬ 43 አመት አስቀድሞ በ1975 መሥርተዋል።
አቶ ፍስሐ ወልደአማኑኤል ለሰብአዊነት ካላቸው ጥልቅ ፍቅር የተነሳም ከዛሬ 25 ዓመት ቀደም ብሎ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች በጤና ፣ በስፖርት እና የሚረዳ ‘አጋር’ የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትን ያቋቋሙ ሲሆን ይህን ማህበር መስርተው ለፍሬ በማብቃታቸው ትልቅ የህሊና እርካታ እንዳገኙ ይናገራሉ።
አቶ ፍሰሐ ወልደአማኑኤል በእግር ኳሱ እና በሰብአዊ እርዳታ ያኖሩት አሻራ ትልቅ መሆኑ ግምት ውስጥ ገብቶ የ7ኛ የጷግሜ ሽልማትን ማግኘታቸው ታውቋል።



Source: GetuTemesgen









No comments yet.