#Ethiopia | በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የተሽከርካሪ ዕቃዎችን የሰረቁ 7 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን የክፍለ ከተማው ዋና ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
ዋና መምሪያው በክፍለ ከተማው ውስጥ ተበራክቶ የነበረውን የመኪና ዕቃዎች ስርቆት ለመግታት እና ወንጀለኞችን በህግ ጥላ ስር ለማዋል በጥናት ላይ የተመሰረተ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል።
ለአንድ ወር ከ15 ቀን በተደረገው በዚህ ክትትል በክፍለ ከተማው እና በሌሎች አካባቢዎች የመኪና ዕቃዎችን ሲሰርቁ የነበሩ 5 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም የተሰረቁ ዕቃዎችን ሲቀበሉ የነበሩ 2 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራቸው እየተጣራ መሆኑን የዋና መምሪያው አዛዥ ኮማንደር አራጌ እሸቴ ገልጸዋል።
ዳዊት መንግስቱ፣ ከድር አህመድ፣ ማሃዲ ሳቢት፣ ኤሊያስ አረጋ እና በቃሉ አንዱአለም የተባሉት ግለሰቦች በተለየ ሁኔታ የመኪና ዕቃዎችን በመስረቅ ወንጀል ላይ ተሰማርተው ይንቀሳቀሱ እንደነበር በበቂ ማስረጃ በመረጋገጡ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም ደረጀ ታደስ እና ቾምቤ ሀይሉ የተባሉት ተጠርጣሪዎች ደግሞ የተሰረቁትን ዕቃዎች ሲገዙ በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው ቀጥሏል።
ተጠርጣሪዎቹ ድርጊቱን ይፈጽሙ የነበረው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች እና ቀናት ከሌሊቱ 7 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን ፖሊስ አረጋግጧል።
በእነዚሁ ግለሰቦች ላይ 11 የምርመራ መዝገቦች የተከፈቱ ሲሆን፣ በሸገር ከተማ መልካ ኖኖ ወረዳ ልዩ ቦታው አንፎ በሚባለው አካባቢ በተሰረቁ ዕቃዎች መቀበያ ሱቅ ላይ በህጋዊ መንገድ በተደረገ ብርበራ በርካታ ንብረቶች ተይዘዋል።
ከእነዚህም መካከል የተሽከርካሪ ጌጅ፣ ስፖኪዮ፣ ዳሽቦርድ፣ የፎቶ ኮፒ ማሽን፣ ኮምፒውተር፣ ወንጀሉን ለመፈጸም ይጠቀሙባቸው የነበሩ 3 ህገወጥ ሽጉጦች ከነሁለት ጥይቶቻቸው፣ መቁረጫ ከተሮች እንዲሁም ኮድ 2 አአ 40817 A.A ዴኤክስ እና ኮድ 3 A 96821 አአ ፕላትስ ተሽከርካሪዎች እንደሚገኙበት ኮማንደር አራጌ አስረድተዋል።
በምርመራው ስፋት ከነባሮቹ 11 መዝገቦች በተጨማሪ በቦሌ፣ ለሚ ኩራ፣ የካ፣ አቃቂ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ተጨማሪ 10 መዝገቦች ተደራጅተው በድምሩ 21 የምርመራ መዝገቦች ክስ ለመመስረት በሂደት ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በክፍለ ከተማው ይስተዋል የነበረው የመኪና ዕቃዎች ስርቆት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ከኃላፊው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።
የፖሊስ አዛዡ ለዚህ ስራ ስኬት ድጋፍ ላደረጉ አካላት እና ጥቆማ በመስጠት ለተባበሩ ህብረተሰብ ክፍሎች በዋና መምሪያው ስም ምስጋና አቅርበዋል።
በመጨረሻም የመኪና ዕቃ የተሰረቀባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ፖሊስ መምሪያ በአካል በመቅረብ ንብረቶቻቸውን መለየት እንደሚችሉ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።
#addisababapolice #crimeprevent #ethiopiapolice #security #addisababa #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን



Source: GetuTemesgen









No comments yet.