የምንመካከረው በብሔራዊ መግባባት አገርን ለማጽናት እንጂ የቡድን የበላይነትን ለማንበርና ሌላ አዲስ የእርስ በእርስ ጦርነት ለ

- Advertisement -
Sidebar AD

የምንመካከረው በብሔራዊ መግባባት አገርን ለማጽናት እንጂ የቡድን የበላይነትን ለማንበርና ሌላ አዲስ የእርስ በእርስ ጦርነት ለማዋለድ አይደለም!

በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ዙሪያ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

ኢትዮጵያ ሀገራችን እያለፈችበት ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት በምክክር ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር አገር ልትጸና ይገባል በሚል ጽኑ እምነት ፓርቲያችን የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል። በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምሥረታው፣ በኮሚሽነሮች አመራረጥና በኮሚሽኑ የአሠራር ሂደት፣ የአካታችነት ችግሮች፣ እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶች በሚያሳድሩት አሉታዊ ተጽዕኖና መሰል አስቻይ ባልሆኑ ሁኔታዎች ላይ ጠንካራ ሀሳቦችንና የመፍትሔ ጥቆማዎችን ፓርቲያችን ሲያቀርብ መቆየቱም ይታወቃል። ፓርቲያችን በምክክሩ ሂደት እና ከምክክሩ አስቀድሞ ስኬታማ ምክክር ለማካሄድ ሊተገበሩ ይገባቸዋል ብሎ የሚያምንባቸውን ሃሳቦችና ቅድመ ሁኔታዎች በግልጽ አስቀምጦ ያለመታከት ሲያሳስብ የቆየ ቢሆንም ሰሚ ጆሮ በመጥፋቱ አገር ባለችበት ሁኔታ ወደ ምክክር እንድትገባ ተደርጓል። እናት ፓርቲ ይህን በትክክለኛው ጎዳና ተጉዞ በስኬታማ መልኩ ሊጠናቀቅ ቢችል የአገራችን መፃኢ ጉዞ ላይ ትልቅ ምዕራፍ ሊከፍት የሚችልን ሂደት ቅድመ ሁኔታዎች ስላልተሟሉ በማለት በቸልታ ሊመለከተው ያልፈለገ ሲሆን ይልቁን ሂደቱ ውስጥ በማሳተፍ ትክክለኛነቱን ካረጋገጠ ለአገር የሚበጁ ሀሳቦችን በማንሳት ለመሞገት ብሎም በተመካካሪዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማድረግ በጎ ተጽዕኖ መፍጠርን በማሰብ በምክክሩ እየተሳተፈ ይገኛል።

አገር የገባችበት ችግር ከምንጊዜውም ይልቅ በተወሳሰበበት ሁኔታ ውስጥ የምክክሩ ሂደት ከነችግሮቹ እያነከሰ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየተሸጋገረ ያለ ቢሆንም በሂደቱ የጎሉ ችግሮች እየተስተዋሉበት ይገኛል። ለአብነትም በወረዳ ደረጃ ተደረጉ ከተባሉ ምክክሮች ጀምሮ የምክክር ተሳታፊዎች የገዥው ፓርቲ አባላት እና የሥርዓቱ ደጋፊዎች መሆናቸው ሲገለጽ የነበረ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ እየተደረገ ባለው በዚህ ምክክርም አብላጫውን ቁጥር የሚይዙ ተሳታፊዎች የገዥው ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች መሆናቸውን መረዳት ችለናል። በምክክሩ ሂደት ድምጾች እንዳይሰሙ መገደብ፣ የአካታችነት ችግሮች፣ የተሳታፊዎች ምርጫና ምደባ፣ የፍትሓዊነት፣ የገለልተኝነት፣ የግልጽነት ማነስ፣ በጸጥታ አካላት ታጅቦ መወያየት፣ የውይይት ተሳትፎውን ለማጥበብ ከውስጥና ከውጭ የሚደረጉ ጫናና ወከባዎች፣ የምክክሩ አጠቃላይ ወለል ወይም ቀይ መሥመር ያለመኖር እና የመሳሰሉ ጉልህ ችግሮች የተስተዋሉበትን እውነታ ታዝበናል።

ምክክሩ ኢትዮጵያን ለማጽናት ሳይሆን እንዳለፈው ጊዜ ስሑት ትርክትና ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ብሎም ሁሉ ለእኔ ብቻ ፍላጎት በአጠቃላይ ኢትዮጵያን አንደ ሀገር እና ዋና መገለጫ ጌጦቿን ኹሉ ለድርድር ያቀረበ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በዚኽም የምክክሩን ፍትሓዊነትና ቅቡልነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆኖ አግኝተነዋል። ይኽ ደግሞ ፓርቲያችንና ሌሎች ተሳታፊዎች ከሂደቱ ራሳቸውን እንዲያገሉ እያስገደደ ይገኛል።

ምክክር የቅንጦት ጊዜ ኹነት ሳይኾን የቀውስ ጊዜ መፍትሔ ማመንጫ ውጥን ነው። ቀዳሚው ዘርና ጎሳ ላይ የተመሠረተው ፌዴራሊዝም ሀገራችንን ሊያጠፋት ከጫፍ ደርሶ እያለ ይህን ያፈጠጠ አደጋ ሊያስቀር ወይም ሊያለዝብ የሚችል መፍትሔ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም ምልክቱ እንኳ አለመታየቱ እጅግ የሚያስቆጭ ነው። እንዲያውም ገና ምክክሩ ሳይጠናቀቅ አንዳንድ ክልሎችን በስም ተጠርተው ሌላ ክልል ለማዋለድ ምክረ ሀሳብ ሲነሳ ብቻ በደስታ ይጨበጨባል፤ ሌላው ደግሞ ማን ነክቶን እያለ በማን አለብኝነት መግለጫ ይሰጣል። ይህም በዘርና በጎሳ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ለሀገር አንድነትና ሕልውና ሥጋት መሆኑን አንዱ ማሳያ ነበር። በሌላ በኩል ይህ ምክክር እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት ቢያንስ ሦስት ክልሎች ላይ ጦርነቶች እየተካሄዱ ነው፤ ሌላውም መጣሁ እያለ ነው። የርስ በርስ ጦርነቱን ጉዳይ ብልጽግናን ጨምሮ ሁሉም ተዋጊ ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ እውነተኛ፣ ጥልቅ ውይይትና ደፋር ምክረ ሀሳብ ይፈልግ የነበረ ቢሆንም ሂደቱ ግን እከከኝ ልከክህ ሆኖ የአንድን ወገን ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ ቀድሞ የተወሰነን ውሳኔ በሀገራዊ ምክክር ስም ቅቡልነት እንዲኖረው ለማድረግ እየተከናወነ ነው። የታሪክና የትርክት መፋለሶች በናኙበት በዚህ ዘመን ቢያንስ እውነት አፈላላጊ ቡድኖችን አዋቅሮ ግማሽ መንገድ እንኳን ማቀራረብ ይገባ ነበር።

እነዚኽንና መሰል አንኳር ጉዳዮች እንጂ የኢትዮጵያ መሪ (ከፕሮቶኮል አንጻር ነው አመክንዮው) ጠቅላይ ሚንስትር ሳይሆን ፕሬዝዳንት መኾን ነው ያለበት ላይ አልነበረም የችግሮቹ ቋጠሮ ያለው። ዙሪያ ዙሪያዋን ሲሏት የነበረችውን አዲስ አበባ በወከባ ብዛት ለአንድ ቡድን ሆ ብሎ ለማሳቀፍና አዲስ የፀብ ግንባር ለመቀስቀስም አልነበረም ለምክክር የተቀመጥነው፡፡ ድሬዳዋ ከየት ወገን ትሑን የሚለው ሀገር ሊያፈርስ ደርሶም አልነበረም በሚሊዮን የሚቆጠር የሀገር ሀብት አባክነን ለምክክር የተቀመጥነው፡፡ በዓለም በልዩነት የምንታወቅበት ዘመን አቆጣጠር አሥሮ ይዞንም አልነበረም ምክክር ያስፈለገን፡፡ በአጠቃላይ የተጠቀሱና መሰል የተስተዋሉ ሳንካዎች ምክክሩ ከታለመለት ዓላማና በሀገሪቱ ያለውን ችግር ከሥሩ ከመፍታት ይልቅ ጠግኖ ለማስቀጠል፣ ለይምሰል የተደረገ፣ የአገዛዝ እና ቡድን(ኖች) ጠባብ ጊዜያዊ ፍላጎት ለማሳካት በሚመስል ሁኔታ እየተከናወነ እንዳለ ይሰማናል። በዚህም በመሠረታዊ የሀገር ሕልውና ጉዳዮች በዋናነት የርስ በርስ ጦርነትን በማስቆም፣ የዘርና ጎሳ ፌዴራሊዝምን ማስቀረት/ማለዘብ እንደ ዋና ግብ መያዝና መሰል የተጋረጡ ፈተናዎች በአግባቡ ተረድቶ እልባት የሚበጅበትን አቅጣጫ ሊያስቀምጥ ያልቻለ ሀገራዊ ምክክር ከመነሻው እንደከሸፈ ለመረዳት ነቢይ መሆን አይጠይቅም።

እናት ፓርቲ ከዚህ በመለስ ባሉ የምክክር አጀንዳዎች እና በምክክር ስም ተላለፉ በሚባሉ ስምምነቶች ላይ ፊርማውን የማያሰፍር መሆኑን ሕዝባችን እንዲያውቅ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡ በዚህም፤

1. ገዥው ፓርቲ በሀገራዊ ምክክሩ ስም ለማሳካት ከሚፈለግ ማንኛውም ፍላጎትና ሀገርን አስይዞ ከሚደረግ የፖለቲካ ቁማር እንዲታቀብ እናሳስባለን።

2. ተመካካሪዎች ለጊዜያዊ ጥቅምና የፖለቲካ ውሳኔዎች ሽፋን ከመስጠት እና በታሪክ ተወቃሽ ከሚያደርጉ ድርጊቶች በመቆጠብ ለሀገርና ለሕዝብ መቆምን በቀረችው አጭር ጊዜም ቢሆን በድፍረት እንዲያሳዩ በአክብሮት እንጠይቃለን።

3. ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገራዊ ምክክሩ የጥቂት አካላትን ፍላጎት ማስፈጸሚያና ለአዲስ ቁርሾ የሚያዘጋጅ እንዳይሆን ሂደቱን በንቃትና በትኩረት እንዲከታተል እናሳስባለን።

ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!

እናት ፓርቲ
ነሐሴ ፮ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ




Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: