የባር እና የአልኮል መጠጥ ቤቶች በስራ ቀናት ከቀኑ 9 ሰዓት በፊት እንዳይከፈቱ ታገደ

- Advertisement -
Sidebar AD

​#FastMereja | የስራ ባህልን ለማሻሻል፣ የስራ ሰዓት ላይ የሚደረግ የአልኮል መጠጥ አጠቃቀምን ለመግታት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚል ባሮችና የአልኮል መጠጥ ማከፋፈያዎች በስራ ቀናት ከቀኑ 9:00 ሰዓት በፊት እንዳይከፈቱ የዩጋንዳ መንግስት ጥብቅ መመሪያ አስተላለፈ።

​የዩጋንዳ የአካባቢ አስተዳደር ሚኒስቴር አዲሱን መመሪያ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ እርምጃው በስራ ሰዓት በሚደረግ የአልኮል መጠጥ አጠቃቀም ምክንያት የሚከሰተውን የስራ ፈትነት፣ የማህበራዊ ህይወት መዛባት እና የወንጀል ድርጊቶች ለመቀነስ ያለመ መሆኑን ገልጿል። በሚኒስትር ባላም ባሩጋሃራ በተፈረመው ደብዳቤ ለአካባቢ አስተዳደሮች፣ ከንቲባዎች እና ለጸጥታ አካላት መመሪያው በአስቸኳይ እንዲያስፈጽሙ ታዟል።

​በዚህ አዲስ ህግ መሰረት ማንኛውም ባር፣ ባህላዊ የመጠጥ ቦታ ወይም አልኮል የሚሸጥ ድርጅት በሳምንቱ የሥራ ቀናት ከቀኑ 9 ሰዓት በፊት አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች ምንም ዓይነት የአልኮል መጠጥ መሸጥ ሙሉ በሙሉ የተከለከለ ሲሆን፣ ይህንን መመሪያ በሚጥሱ ነጋዴዎች እና ድርጅቶች ላይ ከባድ ህጋዊ እርምጃ እና የእስራት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተገልጿል።

​የአካባቢ አስተዳደር እና የጸጥታ አካላት መመሪያውን ሳይተገብሩ በሚቀሩ ወይም ህጉን በተደጋጋሚ በሚጥሱ የንግድ ተቋማት ላይ የንግድ ፈቃድ የመሰረዝ እና ድርጅቶቹን እስከመጨረሻው የመዝጋት ስልጣን ተሰጥቷቸዋል። ውሳኔው በሀገሪቱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ሰፊ ውይይት ያስነሳ ሲሆን፣ አንዳንዶች እርምጃውን የዜጎችን ስነ-ምግባር እና ምርታማነት ለማሻሻል ጠቃሚ ነው ሲሉ ሲደግፉት፣ ሌሎች ደግሞ በትግበራው ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተደራሽነት እና ቁጥጥር ተጋላጭነቶችን በማንሳት አስተያየት እየሰጡበት ይገኛሉ።


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2