80 ዓመት ኩራት፤ 80 ዓመት ትሕትና — የኢትዮጵያ አየር መንገድ!

- Advertisement -
Sidebar AD

(የኢትዮጵያ አየር መንገድን 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል አስመልክቶ የተጻፈ)

ተስፋዬ እሸቱ (ረዳት ፕሮፌሰር)
ሮም፣ ጣሊያን

#Ethiopia | “የኢትዮጵያ አየር መንገድ” የሚለው ዓለም አቀፍ ዝና ያለው ስያሜ ለእኔ በደማቅ ወርቃማ ቀለም የተጻፈ የክብር ስሜ ነው። ለእኔ ብቻም ሳይሆን፣ ለአንተም፣ ለአንቺም፣ ለእሱም፣ ለእሷም፣ ለእነሱም… ለሁላችንም ዓለም አቀፍ ታላቅነትን ያጎናጸፈን የወል መለያ፣ የክብር ስማችን ነው።

ክብርና ኩራታችን የሆነው ይህ ታላቅ አየር መንገዳችን፣ በዓለም ሁሉ የእኛ የኢትዮጵያውያን ባለሙሉ ሥልጣን ልዩ ልዑክ፤ የምድርና የሰማይ ወኪል እንደራሴም ነው።

የአየር መንገዳችን ታሪክ የአንድ ተቋም ታሪክ ብቻ አይደለም። አንድ ሕዝብ ራሱን ለዓለም ያስተዋወቀበት፣ የገለጠበት ታሪክ ነው፤ ልክ እንደ አድዋ በዓለም ላይ ያልተሸነፍንበት ታሪካችን ነው።

ለዚህም ነው “የኢትዮጵያ አየር መንገድ” ስለተባለው የማንነታችን ልዩ ምልክት ዕድሜዬን ሙሉ ብጽፍ የማይሰለቸኝ።

አንዳንድ ተቋማት ትርፍ ብቻ ሊያጋብሱ ይችላሉ፤ እሰየው ነው። አንዳንዶች ደግሞ ከትርፍ በላይ የሀገርን ክብር በኩራት ይሸከማሉ፤ ይሄማ ሲሆን ይበልጥ መታደል ነው።

ታዲያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገርን ክብር የተሸከመ፣ ላለፉት ሰማንያ ዓመታት ሳይታክት፣ ሳይዛነፍ የኩራታችን ምንጭ የሆነ፣ በአልማዝ ያጌጠ ስማችን ነው።

ለ80 ዓመታት ተሳፋሪን ከነሻንጣው ብቻ አላጓጓዘም፤ የአፍሪካን ተስፋ፣ የኢትዮጵያን ስም፣ የጥራትን ልክ ተሸክሞ የበረረ ኩራታችን ነው።

ኩራት ከተደጋጋሚ ስኬት ይወለዳል።

አንድ ጊዜ ተወዳድሮ ማሸነፍ ክስተትም ዕድልም ሊሆን ይችላል፤ ለ80 ዓመታት ግን በዓለም የአቪዬሽን ገበያ ውስጥ ተወዳድሮ መቆየትና ለአንድ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለአንድ አህጉር የኩራት ምንጭ መሆን ክስተት አይደለም፤ ዕድልም ሊሆን አይችልም።

ያ ራዕይ ነው።
ያ ፕሮፌሽናሊዝም ነው።
ያ ተቋማዊ ባህል ነው።
ያ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ የሥራ ሥነ-ምግባር ነው።
ያ እንደ አድዋ ድል የማይበገር ጽናትን በዘመናዊ ውድድር ውስጥ በአዲስ መልክ የገለጠ የቆራጥነት መንፈስ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእኛ ኩራት የሆነው ከፍ ብሎ ስለበረረ ብቻ አይደለም፤ ለ80 ዓመታት ከፍ ብሎ መቆየት ስለቻለ ነው።

የኩራታችን መሠረቱም በተለዋዋጭ ቴክኖሎጂ፣ በማይገመት የዓለም ኢኮኖሚ፣ በከባድ ዓለም አቀፍ ውድድር፣ በተለያዩ ችግሮችና ፈተናዎች መካከል ስሙን ጠብቆ መጓዝ በመቻሉ ነው።

ስለዚህ “80 ዓመት ኩራት” ስል በተቋሙ የተቆጠረውን 80 ዓመት ብቻ ማለቴ አይደለም።

80 ዓመት ያልተቋረጠ ብቃት፤
80 ዓመት ተጠብቆ የኖረ ስም፤
80 ዓመት ያልተሸነፈ ተወዳዳሪነት፤
80 ዓመት የተገነባ እምነት ማለቴ ነው።

ላለፉት ሰማንያ ዓመታት ተከብሮ አስከብሮናል።

ሌላው፣ ብዙ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲወራ ያገኛቸውን ሽልማቶች፣ የሚያስመዘግበውን ትርፍ፣ የሚገዛቸውን ዘመናዊ አውሮፕላኖችና የሚደርስባቸውን ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች እንቆጥራለን።

ነገር ግን በሰማንያ ዓመት ታሪኩ ውስጥ አንድ የተዘነጋ፣ ወይም በበቂ ሁኔታ ጎልቶ ያልወጣ ጌጥ ያለው ይመስለኛል።

በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳፋሪዎችን በአንድ ቃል የሚቀበልበትና የሚሸኝበት፤ የኢትዮጵያዊ ትሕትና ተግባራዊ መገለጫ፤ የእኛ የኢትዮጵያውያን የአክብሮትና የመስተንግዶ ባህል ማሳያ፦

“አንቱ!”

“አንቱ…” የሚለው ቃል በጣም አጭር፣ ሲሰሙትም ቀላል ይመስላል። ሆኖም የተሸከመው ሥልጣኔ ትልቅ ነው።

በአማርኛ “አንተ” እና “አንቱ” መካከል ያለው ልዩነት የሰዋስው ልዩነት ብቻ አይመስለኝም፤ የአመለካከት፣ የክብርና የማኅበራዊ ግንኙነት ልዩነትም አለው።

“አንቱ” ማለት፣ “እርስዎ ዋጋ አለዎት” እንደማለት ነው።

“አንቱ” ማለት፣ “የተከበሩ ነዎት” እንደማለትም ነው።

ታዲያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህን ኢትዮጵያዊ ከበሬታና ትሕትና በየቀኑ ለዓለም አስተዋውቋል፤ አስተምሯል።

አቤት ትሕትና በአየር መንገዱ ሠራተኞች ላይ ሲያምር!

ትሕትና መልክ ቢኖረው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ይመስል ነበር።

በዚህም በየቀኑ የሚሸጠው ቲኬት ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያዊ የሆነውን፣ እንግዶችን በትሕትና ተቀብሎ በፍቅር የማስተናገድ ባህልንም ጭምር እንጂ!

80 ዓመታት ሙሉ ኢትዮጵያውያን ለሰው ልጅ ክብር የሰጡበትን ባህል በደመና ላይ ሳይቀር ይዞት ሲበር፣ ሲያኮራን ኖሯል።

አዎ! 80 ዓመት ኩራት፤ 80 ዓመት ትሕትና!

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ውጭ በሌላ በምንም መልኩ እንደዚህ ተገልጦ አላየሁም፤ አልተሰማኝምም!

ዘለዓለማዊ ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ!

መልካም 80ኛ ዓመት!





Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: